Fana: At a Speed of Life!

በአምቦ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት 29 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምቦ ከተማ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት በ29 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን ፓሊስ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርደሳ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና ለለውጥ አመራሩ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት 29 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል 28ቱ ህክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ ቀሪው ግለሰብ በአምቦ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘም ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የተናገሩት።

በተመሳሳይ ከትናንት በስቲያ በቡራዩ ከተማ በተከሰተውና ለከተማው የአስተዳደርና የጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ሰለሞን ታደሰ ግድያና ከሌሎች ሶስት ሰዎች መቁሰል ጋር በተያያዘ 17 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

በሃይማኖት እያሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.