Fana: At a Speed of Life!

በአርቲስት ሀጫሉ ግድያ የተጠረጠረው ከበደ ገመቹ ፍርድ ቤት ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረውና ሸሽቶ በሃምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም አዳአ ድሬ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋለው ከበደ ገመቹ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረበ።

በዛሬው የችሎት ውሎም መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ በተጠርጣሪው ላይ የሰራውን ምርመራ ስራ ገልጿል።

በዚህ ጊዜም ከተጠርጣሪው እጅ ላይ ከተገኘው ስልክ የድምጽ እና የመልዕክት ልውውጥ ከኢትዮ ቴሌኮም በማስመጣት በርካታ ማስረጃ ማሰባሰቡን ለችሎቱ አብራርቷል።

በእጁ ላይ የተገኘው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ ለምርመራ መላኩን ያብራራው መርማሪ ፖሊስ፥ በዛሬው ችሎት መገለጽ የሌለባቸው ከበስተጀርባ ያሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምርመራዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጿል።
በዚህ መልኩ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች ተጨማሪ ምርመራዎች 14 ቀን እንዲሰጠውም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በአስተርጓሚ አስተያየት ካለው እንዲያቀርብ የተጠየቀ ቢሆንም፥ ምንም አይነት አስተያየት እንደሌለው ምላሽ ሰጥቷል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም ለተጨማሪ መርመራ ለፖሊስ 14 ቀን በመፍቀድ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለነሃሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተያያዘ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ቃለ መጠየቅ በማድረግ ፕሮግራሙን ቆርጦ በማቅረብ፤ እንዲሁም ሰኔ 22 እና 23 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦ.ኤም.ኤን) አመጽና ብጥብጥ እንዲነሳ በመቀስቀስ የተጠረጠረው ጋዜጠኛ ጉዩ ዋርዮም ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠርጣሪው ጋዜጠኛ ከላይ በተጠቀሰው ሚዲያ አመጽ እንዲነሳ ቅስቀሳ ማድረጉን የሚያስረዳ የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡን እና ተጨማሪ የምስክር ቃል መቀበሉን ተናግሯል።

በእጁ ላይ የተገኘ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በፎረንሲክ እያስመረመረ መሆኑንም መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሰልጣን እና ከተለያዩ ተቋማት ማስረጃ ለማሰባሰብና ቀሪ ምርመራ ለመስራት ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም የምርመራ መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነሃሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.