Fana: At a Speed of Life!

በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠሩት ጥላሁን ያሚና አብዲ አለማየሁ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ቀደም ሲል በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን በተመለከተ ባወጣነው ዘገባ ተጠርጣሪ ጥላሁን ያሚ ተልዕኮውን ስለሰጠው አካል እውነተኛውን መረጃ ለመናገር ጥበቃ ይደረግልኝ ሲል ጥያቄ አቅርቧል በሚል ያካተትነው መረጃ ስህተት መሆኑን እየገለፅን ትክክለኛው አገላለፅ ለቤተሰቦቹ ጥበቃ እንዲደረግ ጠየቀ የሚለው መሆኑን እንገለፃለን፡፡ ለተፈጠረው ስህተትም አንባቢያንን እና የሚመለከታቸው አካላትን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

የተስተካከለው ሙሉ ዜናም እንደሚከተለው ቀርቧል

በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠሩት ጥላሁን ያሚና አብዲ አለማየሁ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት ጥላሁን ያሚና አብዲ አለማየሁ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደሉን ተከትሎ በግድያ ወንጀል የተጠረጠሩት ጥላሁን ያሚ እና አብዲ አለማየሁ ለሶስተኛ ጊዜ ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በተሰጠው የተጨማሪ ስምንት ቀን ጊዜ የሰራውን የምርመራ ስራ የገለጸ ቢሆንም በዋናነት ከተጠርጣሪዎች ጋር በግድያ ዙሪያ የተጠረጠሩት ላይም ምርመራ ማድረግ ጀምሯል፡፡

የስልክ ግንኙነትን በተመለከተም ቃል የመቀበል ስራ መስራቱንም አስታውቋል፡፡ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም የተላከ የስልክ መልዕክት ሰፊ መሆኑን ተከትሎ የትንተና ስራ እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

ከተጠርጣሪዎች እጅ የተገኙ ስልኮችን ለብሄራዊ መረጃ ደህንነት በመላክ ሌሎች የምርመራ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግሯል መርማሪ ፖሊስ፡፡

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ከዚህ በፊት ከሰራችሁት ስራ ውጭ ምን የተለየ ውጤት ተገኘ ሲል ላቀረበው ጥያቄ መርማሪ ፖሊስ ከተጠርጣሪዎች በስተጀርባ ሌሎች ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የሚያመላክት መረጃ መገኘቱን ጠቅሷል፡፡

እንዲሁም ከወንጀሉ በስተጀርባ የተቀነባበረ ወንጀልን ለመለየት ስራ ላይ መሆኑን የተናገረው መርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪ ጥላሁን ያሚ በበኩሉ ተልዕኮውን ስለሰጠው አካል እውነተኛውን መረጃ ለመናገር ለቤተሰቦቹ ጥበቃ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ሁለተኛ ተጠርጣሪ አብዲ አለማየሁ በተመሳሳይ የእጅ ካቴና ይፈታልኝ ሲል አመልክቷል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ በተደጋጋሚ የራስ ማጥፋት ሙከራ መፈጸሙን ተከትሎ ካቴናው መደረጉን ገልጿል፡፡

መርማሪ ፖሊስም አንደኛ ተጠርጣሪ ደህንነቱን ታሳቢ በማድረግ በምርመራ ክፍል ውስጥ እንዲቆይ መደረጉን ተናግሯል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተጨማሪ ምርመራ በፖሊስ እንደሚያስፈልግ ግምት ውስጥ በማስገባት 11 ቀን በመፍቀድ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለነሃሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.