Fana: At a Speed of Life!

በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ከ30 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታ ተሰረዘ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ከ30 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታ መሰረዙን የፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በጤና ሚኒስቴር ግዥ ጠያቂነት የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ2014 በጀት ዓመት የወባ መከላከያ አጎበር ግዥ ለመፈጸም ከ30 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም አቀፍ የጨረታ የግዥ ሂደት ህግን የተከተለ ባለመሆኑ ጨረታው መሰረዙን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በቀረበለት ጥቆማ መሰረትየጨረታው አሸናፊ ተደርጎ የተመረጠው ድርጅት የአገር ውስጥ የወባ መከላከያ አጎበር የማረጋገጫ ፍቃድ የሚሰጡና የሚያድሱ አካላት ኃላፊነት በግልፅ አለመቀመጡን እንደ ምክንያት አድርጎ በመውሰድ ካስቀመጣቸው ሶስት ወኪሎች በአንደኛው ተወካይ ህግን ባልተከተለ መልኩ በተጭበረበረ ሁኔታ ህገ-ወጥ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የወሰደና በጨረታው እንዳይወዳደር የተሰረዘበት መሆኑን አረጋግጧል።
ሆኖም በሌላኛው ተወካይ በተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት በመወዳደር የጨረታው አሸናፊ እንዲሆን መደረጉ፣ የዋናውን ድርጅት ከተጠያቅነት እንደማያድነውና የግዥው ሂደት ጤናማ አለመሆኑን ኮሚሽኑ ከማጣራት ሂደቱ መረዳቱን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ በአካሄደው የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራና ባረጋገጣቸው ግኝቶች ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ግዥውን ከሚፈፅመው ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ መያዙን አስረድቷል፡፡
ይህ ከ30 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው አለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ግዥ ለ17 ሚሊየን 809 ሺህ 388 የወባ መከላከያ አጎበሮች ግዢ ጨረታ የወጣ ሲሆን÷ ሂደቱ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ስለመሆኑ በማጣራት ግኝቱ የማስተካከያ ምክረ ሀሳቦችን የያዘ ሪፖርት ለጤና ሚኒስቴር እና ከላይ ለተመለከቱት መንግሥታዊ ተቋማት ማሳወቁን አብራርቷል፡፡
ከዚህ በመነሳት የጤና ሚኒስቴር ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ የጨረታ ሂደቱ በተጭበረበረ ሰነድ መሆኑን ያረጋገጠውን የዓለም አቀፍ ጨረታ ማስቀጠል በግዥው ሂደት ላይ የነበረን ስጋት እንዲቀጥል የሚያደርግና ውጤቱ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሉታዊ ተፅኖ ሊፈጠር እንደሚችል በመጥቀስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጨረታውን መሰረዙን አስታውቋል፡፡
ይህንኑ ውሳኔ ተጫራቾች እንዲያውቁት እንዲደረግ ለኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ማሳወቁንም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡
ኮሚሽኑ ያቀረበው ምክረ ሀሳብ ተቋማት ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በራስ ውሳኔ ወደ መከላከል የሚያደርስ በመሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ይህንኑ ምክረ ሀሳብ በመቀበል የእርምት እርምጃ መውሰዱ አርያነት ያለው ተግባር ነው፡፡
ዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታውን በተመለከተ ፥ የግዥ ሂደቱ “ህግን የተከተለ አይደለም ” የሚል ጥቆማ ለፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቀርቦ፥ ከየካቲት 8 እስከ 24 ቀን 2014 ዓ.ም በአስቸኳይ የሙስና መከላከል የማጣራት ሥራ ማከናወኑንም ኮሚሽኑ አውስቷል፡፡
የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ግንቦት 11 ባወጣው ምግለጫ በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታ መሰረዙን ማስታወቁና ይህንኑ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ኮሚሽኑ የቁጥር ማስተካከያ በማድረግ 300 ሚሊየን ሳይሆን 30 ሚሊየን ዶላር መሆኑን በመግለፅ እርማት አድርጓል። ይህንንም መሰረት በማድረግ በዜናው ላይ እርማት መደረጉን እንገልፃለን።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.