Fana: At a Speed of Life!

በአቡዳቢ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት 14 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተሰበሰበ

 

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 29፣ 2013 ( ኤፍ ቢ ሲ) አቡዳቢ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማኅበር የአመራር ቦርድ አባላት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማፍረስና ህዝቦቿን ለመበተን አልመውና አቅደው የከፈቱብን ጦርነት ሀገርን፣ ህዝብንና መንግስትን በእጅጉ እየተፈታተነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና አገራችንን ለመታደግ የሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

በተያያዘም አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በውይይቱ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዉ፣ ለዚህም በአቡዳቢ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማኅበራት ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በዚሁ መሰረት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማኅበር የአመራር ቦርድ አባላት በዕለቱ ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ከከሃዲ አሸባሪዎች ጋር እያደረገ ያለውን ተጋድሎ በማድነቅ ለሰራዊቱ ድጋፍ ይሆን ዘንድ ብር 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል።

በተመሳሳይ በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማህበር ቦርድ ባደረገው ሰብሰባ ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ድጋፍ እንዲሆን መለገሱ ይታወሳል።

በተጨማሪም በአቡዳቢ የሚገኙ ዲፕሎማቶች 1 ነጥብ 3  ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

በአጠቃላይ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሚኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በድምሩ 14 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ድጋፍ ማሰባሰብ መቻላቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.