Fana: At a Speed of Life!

በአቶ ሃምዛ ቦረና መዝገብ የተካተቱ 9 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ከሰአት ፍርድ ቤት ቀርበዋል

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 29 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአቶ ሃምዛ ቦረና (ሃምዛ አዳነ) መዝገብ የተካተቱ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ከሰአት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ ሃምዛ ቦረና (ሃምዛ አዳነ) ፣ ያለምወርቅ አሰፋ፣ ታምራት ሁሴን ፣ ሰበቃ ቃርቴ እና ጌቱ ተረፈን ጨምሮ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ ስምንቱ የአቶ ጃዋር ዋና ጠባቂዎች ወይም አጃቢዎች ናቸው።

በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት ለአራተኛ ጊዜ በቀረቡ በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሰራውን የምርመራ ስራ አቅርቧል።

አቶ ሃምዛ በተጠረጠሩበት ጉዳይ የቪዲዮ ምስል መሰብሰቡን የተናገረው መርማሪ ፖሊስ የአቶ ጃዋር ጠባቂዎች በተጠረጠሩበት ጉዳይ ደግሞ 27 ምስክሮችን መቀበሉን ተናግሯል።

ከተጠርጣሪዎች እጅ የተያዘው መሳሪያም የፎረንሲክ ምርመራ እንደተደረገለት ነው ፓሊስ ያስታወቀው።

ይህን ምርመራ ማጠናቀቁን በማመላከት ዐቃቤ ህግ በአራዳ ምድብ ችሎት የከፈተውን የቅድመ ምርመራ መዝገብ እንዲቀጥል ጠይቋል።

አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ ሃምዛም በተጠረጠሩበት ጉዳይ ላይ ግንኙነት እንደሌላቸው መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን÷ የአቶ ጃዋር ጠባቂዎች ጠበቆችም ደንበኞቻችን በተመሳሳይ የወንጀል ተሳትፎ የላቸውም ሲሉ መቃወሚያ በማሰማት በዋስ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከእስር ቤት ቆይታቸው ጋር ተያይዞ በተለይም ከቤተሰብ ጥየቃ ጋር በድጋሚ አቤቱታ አስመዝግበዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግም በተጠርጣሪ ጠበቆች በተነሱ መቃወሚያ እና በእስር ቤት ከቤተሰብ ጋር አልተገናኘንም የሚል ለቀረቡት አቤቱታዎች ቀርቦ ምላሽ ሰጥቷል።

የቅድመ ምርመራ መዝገብ የከፈተ መሆኑን የገለፀው ዐቃቤ ህግ በዛው መዝገብ ተጠርጣሪዎቹ እንዲቀርቡለት ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹም ሆኑ ጠበቆቻቸው በማንኛውም ሚዲያ ላይ ምንም አይነት አቤቱታ ባያስመዘግቡም ፍርድ ቤቱ በችሎት ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተቋማትን ማንነት በመጠየቅ በውስጥም ሆነ በውጭም ያሉ መገናኛ ብዙሃን በምርመራ ዝርዝር ውጤት ይዘት እና የችሎቱ ክርክሮችን ለህዝብ ማቅረብ አትችሉም ፤ ለችሎት ግብአት እንጂ ፖሊስ ያሰባሰባቸውን ማስረጃዎችም ዝርዝር ይዘት የችሎቱ ክርክር እንዳይቀረብ ሲል አዟል።

ከዚህ በፊት በተሰጠ ትዕዛዝ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ከቤተሰብ ጋር እንዲያገናኛቸው የታዘዘውን ተግባራዊ ባለመሆኑ አሁንም ትዕዛዙ ተግባራዊ እንዲደረግ አዟል።

ይሁንና ከዚህ በፊት በሶስት የጊዜ ቀጠሮ የእነ ሃምዛ መዝገብንም ሆነ የሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ የሰራውን የምርመራ ውጤት እና የተጠርጣሪዎችን መቃወሚያና አቤቱታ እንዲሁም ክርክሮችን ለህዝብ ስናቀርብ መቆየታችን ይታወሳል።

በዚህ በዛሬው ትዕዛዝ መሰረት የዛሬ ችሎት የፖሊስ ምርመራ ውጤት እና ክርክሮች የማይቀርቡ ይሆናል።

ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪዎች የዋስትና ጥያቄ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.