Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትን ለማስጀመር የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ ነው- ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን የታላቁ ህዳሴ ግድብ በቀጣይ ውሃ ሙሌትን ለማስጀምር የሚያስችል ወሳኝ የግንባታ ምዕራፍ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አስታወቁ፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ከፍተኛ የመንግሥት ስራ ሃላፊዎች ቡድን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተያዘት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ውሃ ለመሙላት የሚያስችለው የግንባታ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

በህዝቡ ሙሉ አቅም እና በመንግስት ጠንካራ ክትትልና ጥብቅ አመራር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወሳኝ የግንባታ ምዕራፍ ላይ መዳረሱን ጠቁመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተቀናጀ ርብርብ በሚካሄደው መልካም የግንባታ አፈፃፀም የመጀመሪያውን ምስራች ለማየት መቃረቡን ገልፀዋል።

የግድቡ ግንባታ በርካታ ውጣ ውረዶችን እያለፈ ወሳኝ የግንባታ ዕድገት ምዕራፍ እንዲደርስ፤ በአስቸጋሪ የአየር ፀባይ በፅናት እየተረባረቡ ለሚገኙት የፕሮጀክቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይ የግንባታ ዘመን ከኮቪድ -19 ወረርሽኝ እንዳያውካቸው ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ህዝብ እና መንግሥት የጣለባቸውን ታሪካዊ ሃላፊነት በድል እንዲወጡ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.