Fana: At a Speed of Life!

በአንድ ወር ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ላይ የመኪና እና የመኖሪያ ቤት ሽያጮች በባንክ በኩል ተፈጽመዋል

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በገዥና ሻጭ መካከል የሚደረገው የገንዘብ ቅብብል በባንክ በኩል ብቻ መሆኑን ተከትሎ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ላይ የመኪና እና የመኖሪያ ቤት ሽያጮች በባንክ በኩል መፈፀማቸውን የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲዉ ከመስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በብድር፣ በሽያጭ እና ስጦታ ውል ላይ የሚካሄዱ ሰነዶችን አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ላይ የአሰራር ለውጥ ማድረጉን አስታውሷል፡፡

የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን ስርዓት ለማስያዝ በመንግስት በኩል የተደረጉ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ኤጀንሲው የአሰራር ማሻሻያ ማድረጉንም ነው ያስታወሰው፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ እንደገለፁት የብር ለውጡን ተከትሎ በገዥና ሻጭ መካከል የሚደረገውን የገንዘብ ቅብብል በባንክ በኩል ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ይህም ያልተገባ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከልና በተዋዋይ ወገኖች መካከል መተማመንን በመፍጠር ህብረተሰቡ በዘመናዊ መልኩ የባንክ አካውንት እንዲኖረውና የፋይናንስ ስርዓቱን ብቻ የተከተለ የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር ይረዳል ተብሏል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ “የገንዘብ ለውጡን ተከትሎ ኤጀንሲው አንዳንድ ሀሰተኛ ሰነዶችን ለመከላከል ከባንኮች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር አብሮ እየሰራ ነው” ብለዋል።

በዚህም ከመስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የ2 ሺህ 797 መኪናዎች ሽያጭ በ1 ቢሊየን 276 ሚሊየን 385 ሺህ 465 በባንክ ተፈፅሟል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የ602 መኖሪያ ቤት ሽያጭ በ1 ቢሊየን 588 ሚሊየን 699 ሺህ 768 በባንክ እንደተፈፀመ ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በአጠቃላይ ከሁለቱ የሽያጭ አይነቶች 2 ቢሊየን 865 ሚሊየን 85 ሺህ 234 ብር በባንክ በኩል ግብይቱ እንዲከናወን ተደርጓል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.