Fana: At a Speed of Life!

በአውሮፓ ከመጠን ያለፈ ውፍረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሪፖርት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ ከመጠን ያለፈ ውፍረት “ወረርሽኝ በሚመስል መልኩ” አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሪፖርት አመላከተ።

ትናንት በተካሄደውና ትኩረቱን ከመጠን በላይ ውፍረት ላይ ባደረገው ስብሰባ ላይ ይፋ የሆነ ሪፖርት በአውሮፓ የዜጎች ውፍረት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አመላክቷል፡፡

አሁን ላይ መጠኑ በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ ነው ያለው ሪፖርቱ፥ የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 2025 ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቀነስ ያስቀመጠውን ግብ በአውሮፓ የሚያሟላ ሃገር ይኖራል ብሎ እንደማይጠበቅም ነው ያመላከተው።

በአውሮፓ በአመት ከመጠን ባለፈ ውፍረት ምክንያት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች ህልፈት ሲዳረጉ 200 ሺህ ዜጎች ደግሞ ለካንሰር መጋለጣቸውንም ነው ያስታወቀው።

በአመት በከመጠን ባለፈ ውፍረት ምክንያት ለካንሰር የሚዳረጉ አውሮፓውያን ቁጥርም በመጪዎቹ አመታት እየጨመረ እንደሚሄድ አስጠንቅቋል።

አሁን ላይ 59 በመቶ አዋቂ አውሮፓውያን ከመጠን ያለፈ ውፍረት ተጠቂ ሲሆኑ፥ 7 ነጥብ 9 በመቶ ወይም 4 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚሆኑ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ህጻናትም የዚሁ ችግር ሰለባ ሆነዋልም ነው ያለው።

እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትም ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንደሚያጋጥማቸው የሚገልፀው ሪፖርቱ፥ በአውሮፓ ከሶስት ህፃናት አንዱ ከመጠን ባለፈ ውፍረት ተጠቂ ነው ተብሏል፡፡

በጉርምስና ላይ ባሉ ወጣቶች ላይ የውፍረት መጠን ስርጭቱ እንደሚቀንስም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ትናንሽ ውሳኔዎች ችግሩን ሊቀርፉ አይችልም ያለው ሪፖርቱ የውፍረት ስርጭቱን ለመግታት አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቷል።

በጣፋጭ መጠጦች ላይ ግብር መጨመር ፣ለልጆች ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን ከማስታወቂያ ማገድ እንዲሁም ጤናማ ምግቦች ላይ ድጎማ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አስገንዝቧል።

ከዚህ ባለፈም ሃገራት ከመጠን በላይ ውፍረትን መቆጣጠር የሚቻልበትን አግባብ በጤና ስርአቱ መዘርጋት ይገባቸዋል ማለቱን አ ር ቲ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.