Fana: At a Speed of Life!

በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሰውን ቀውስ ለመግታት የኢነርጂ ምንጭን ወደ ታዳሽ ኢነርጂ መለወጥ ያስፈልጋል- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየደረሰ ያለውን ቀውስ ለመግታት በተባበሩት መንግስታት ከተለዩት ዘርፎች አንዱ የሆነውን የኢነርጂ ምንጭን በፍጥነት ወደ ታዳሽ ኢነርጂ መለወጥ እንደሆነ የውሃ የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አስታወቁ።

በኢነርጂ ሽግግር ዙርያ የሚመክር ተከታታይነት ያለው የበይነ መረብ ውይይት በትናንትናው እለት መካሄድ ጀምሯል።

የበይነ መረብ ውይይቱ “ከአየር ንብረት እንቅስቃሴ ስብሰባ እስከ አረንጓዴ መልሶ ማገገም የኃይል ሽግግርን እንዴት ማግኘት ይቻላል” በሚል መሪ ቃል እስከ መስከረም 7 2013 ዓ.ም ቀጥሎ እንደሚካሄድም ከውሃ መስኖና ኢነጅሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በውይይቱ ላይም የኢፌዴሪ የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ፣ የዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ራስሙሰ ፕሪህን፣ የዴንማርክ የአየር ንብረት፣ ኢነርጂና አገልግሎቶች ሚኒስትር ዳን ጆርገንሰን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል።

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ ውይይቱ እየተካሄደ ያለው በምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች በኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በኬንያና ዩጋንዳ ባልተለመደ ሁኔታ እየዘነበ ባለ ዝናብ በተፈጠረ አውዳሚ ጎርፍ ምክንያት በርካታ ሰዎች ከቀያቸው በተፈናቀሉበት፤ የዓለም ሙቀት መጠን መጨመር እየታየ ባለበት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶች እጅግ በፍጥነት እየተመናመኑ በመጡበት ጊዜ እንደሆነ አንስተዋል።

ይህም የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች ኑሮና በአካባቢያቸው ላይ እያሳደረ ያለው ተጽኖ በግልፅ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየደረሰ ያለውን ቀውስን ለመግታትም በተባበሩት መንግስታት ከተለዩት ዘርፎች አንዱ የኢነርጂ ምንጭን በፍጥነት ወደ ታዳሽ ኢነርጂ መለወጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያና ዴንማርክ በትብብር የኢነርጂ ሽግግሩን በተሻለ ሁኔታ እያከናወኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ኮቪድ 19 እያደረሰ ያለው ጉዳትና ከባድ ተጽኖ እንዲሁም የአየር ንብት ለውጥ በኢትዮጵያም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢነርጂ ሽግግሩን ለማረጋገጥ እርግጠኛ መሆን እንደማያስችል ገልጸዋል።

በትናንትናው እለት መካሄድ የጀመረው የበይነ መረብ ውይይቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አማካኝነት ከተካሄደውና በአየር ንብረት ለውጥና መወሰድ ስላለባቸው ርምጃዎች ከሚመክረው ስብሰባ በኋላ እስካሁን ባለው አንድ ዓመት የኢነርጂ ሽግግርን አስመልክቶ የታዩ ለውጦችና መልካም አጋጣሚዎች እንዲሁም ተግዳሮቶችን በሚመለከት ተወያዮቹ ተሞክሮ የሚለዋወጡትና ወደፊት መደረግ ስላለባቸው ምልከታቸውን የሚገልጹበት እንደሆነ ተገልጿል።

በተለይም ከኮቪድ 19 ለማገገምና የኢነጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ የሚቻልባቸውን መንገዶች የሚጠቁሙበት መድረክ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.