Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተስተዋለው የነዳጅ እጥረት ብዙዎችን ለእንግልት እየዳረገ ነው

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 13፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በትላልቅ የክልል ከተሞች የተስተዋለው የነዳጅ አቅርቦት ችግር የብዙዎችን እንቅስቃሴ እያስተጓጎለ ነው።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአዲስ አበባ ቅኝት ባደረገባቸው የነዳጅ ማደያዎች የአቅርቦት ችግር መኖሩን ለመታዘብ ችሏል።

በሰንጋ ተራ፣ ለገሃር፣ ሜክሲኮ እና ጥቁር አንበሳ አካባቢዎች በተደረገው ምልከታ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የነዳጅ ማደያዎችም ነበሩ፤ በክልል ከተሞችም ተመሳሳይ ችግር ተስተውሏል።

ያነጋገርናቸው የነዳጅ ማደያ ሃላፊዎች የእጠረቱን ምክንያት አናውቅም ብለዋል።

የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አለማየሁ ጸጋዬ፥ በጅቡቲ እና በሱዳን በኩል የሚገባው ነዳጅ እጥረት የሌለበት መሆኑን በመግለፅ፥ እንደ ከዚህ ቀደሙ በየቀኑ ከ300 መኪናዎች በላይ ነዳጅ እየጫኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች በትክክል ስለመጫናቸው እንጂ፥ ስለመድረሳቸው የሚከታተልበት ህጋዊ ሃላፊነት የለበትም ብለዋል አቶ አለማየሁ ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የማዕድን፣ ነዳጅ የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በበኩላቸው የነዳጅ ስርጭትን ለመቆጣጠር ህጋዊ ሃላፊነት እንደሌለባቸው ምላሽ ሰጥተውናል።

የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ማቋቋሚያ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢፀድቅም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገና እንዳልተቋቋመ የሚናገሩት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያ እና ድርጅት ኢንስፔክሽንና ሪጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት ናቸው።

ሆኖም የሚቋቋመው ባለስልጣን ለንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪ ይሆናል ያሉት አቶ ካሳሁን፥ አሁን ላይ መስሪያ ቤታቸው ድጋፍ ከመስጠት ውጪ ሃላፊነት የለበትም ይላሉ።

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላን፤ የነዳጅ አቅርቦት ስርጭት እና ንግድ፣ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር ወደተቋቋመው ባለስልጣን ከ2011 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በመዛወሩ የዕቅዳችን አካል አላደረግነውም ብለዋል። አሁን ላይ የተፈጠረውም ችግር መስሪያ ቤታችንን አይመለከትም ነው ያሉት።

የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ችግሩ መንስኤ ለማጥናት ሃላፊነት የወሰደ የመንግስት አካል የለም። በባለድርሻ መስሪያ ቤቶቹ በኩል የሰሚ ሰሚ መረጃ እንደ ምክንያት የሚቀርበው ለዚሁ ነው።

በአዲስ አበባ የተፈጠረው የነዳጅ አቅርቦት ችግር ሃላፊነት የሚወስድ የመንግስት አካል ጠፍቷል። ተሽከርካሪዎቻቸውን ለሰዓታት በወረፋ ያሰለፉ ዜጎች፣ እንቅሰቃሴያቸው ቆሟል። ባለቤት ባጣው የነዳጅ አቅርቦት ችግር ምክንያት ከጊዜአቸው ባሻገር ከኑሮአቸውም የሚጎድል ነገር እንዳለ ይናገራሉ።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያ እና ድርጅት ኢንስፔክሽንና ሪጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ለውይይት እንቀመጣለን ብለዋል።

 

በርስቴ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.