Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ቢሮ በመከራየት የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ፅህፈት ቤት ስራን በህገ-ወጥ መንገድ ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ቢሮ በመከራየት የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ፅህፈት ቤት ስራን በህገ-ወጥ መንገድ ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

እንደ ኮሚሽኑ መረጃ ከተጠርጣሪዎቹ አንደኛው ግለሰብ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ውስጥ 1 ሺህ 816 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ከመንግስት በሊዝ ለመውሰድ ከዓመታት በፊት እንቅስቃሴ ቢጀምርም መሬቱን ለማግኘት የሚጠበቅበትን ህጋዊ አሰራር መፈፀም ባለመቻሉ መሬቱን አልወሰደም።

ኮሚሽኑ እንዳስረዳው ይኸው ግለሰብ ከአመታት በኋላ መሬቱን በህገወጥ መንገድ እጁ ለማስገባት ከደላሎች ጋር ይነጋገራል።

ይህን ህገወጥ ተግባር ለመፈፀም የተዘጋጁ ግለሰቦች በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ሃያ ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የአብ ህንፃ ላይ ቢሮ በመከራየት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክ እና ማስተላለፍ ፅህፈት ቤት ማህተም፣ የሃላፊዎች የስም ቲተር እና የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶችን እየተጠቀሙ እንደነበረ ነው ያመለከተው።

ወረዳ 2 ውስጥ የሚገኘው መሬት በህገወጥ መንገድ በሊዝ ለመውሰድ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግለሰብ የሊዙን ቅድመ ክፍያ ከፍሎ ውል መዋዋል እንደሚችል የሚገልፅ የፅህፈት ቤት ሃላፊ ስም እና ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤ እጅ ላይ በማስገባት ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት ከቀኑ 5፡00 ሰዓት “ክብ ማህተም የሚደረገው ዋናው መስሪያ ቤት ነው” ተብሎ ወደ አዲስ አበባ መሬት ልማት ማኔጅመንት ዋናው ቢሮ ደርሶ ማህተም ለማስመታት ወደ መዝገብ ቤት ሲገባ የሃላፊውን ፊርማ እና የስም ቲተር የተመለከቱት የመዝገብ ቤቱ ሰራተኛ ተጠራጥረው ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ በቁጥጥር ስር እንዲውል አድርገዋል።

ፖሊስ በአቋራጭ ለመበልፀግ ቢሮ ከፍተው ህገወጥ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩትን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን አስታውቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ በተቋሙ የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች እጅ ሊኖርበት እንደሚችል በመጠቆም ምርመራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፖሊስ አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.