Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከባድ የዘረፋና የግድያ ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩ 70 ግለሰቦች በቀጥጥር ስር ዋሉ

በአዲስ አበባ በተደራጀ ሁኔታው አቅደው ከባድ የዘረፋና የግድያ ወንጀል ፈፅመዋል ያላቸውን 70 እንዲሁም በዘረፋ ወንጀል ላይ የተገኙ 34 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ አበባ ከተማን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ባካሄደው የአንድ ወር የተቀናጀ ኦፕሬሽን በርካታ ተግባራት ማከናወኑን  ገልጿል።

በዚህም ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በተካሄደው ዘመቻ በተደራጀ አኳኃን አቅደው ከባድ የዘረፋና የግድያ ወንጀል ፈፅመዋል ያላቸውን 70 እንዲሁም በዘረፋ ወንጀል ላይ የተገኙ 34 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የገለፀው።

በተጨማሪም በዚሁ የወንጀል ተግባር ትስስር ያላቸው የተያዙ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች 4 ቦንብ፣ 23 ሽጉጦችና 4 ክላሽንኮቭ ጠመንጃና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ናቸው።

እንዲሁም 3 ሺህ 580 የሽጉጥ፣ 200 የብሬን እና 3 ሺህ 171 የክላሽንኮቭ ጠመንጃ በድምሩ 6 ሺህ 951 ጥይቶችን መያዙን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለዚሁ ተግባር ማስፈፀሚያ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 906 ሺህ 40 ብር እና 8 ሺህ 382 የአሜሪካ ዶላርም እንደያዘም ነው ያስታወቀው።

በተመሳሳይ ጁንታው በፈፀመው ጥቃት የተሳተፉና በተለያዩ መንገዶች አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በወንጀል ተግባር መሳተፋቸው በህዝብ ጥቆማ የተደረሰባቸው 170 ተጠርጣሪዎችና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው 53 የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው  በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ በፌዴራል ፖሊስና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች በጥምረት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በሌላም በኩል የተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች በከተማዋ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር  እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ፖሊስ በመረጃ ማረጋገጡን የገለፀው ኮሚሽኑ ማንኛውንም የፀረ-ሰላም ቡድን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያስችል ብቃትና ዝግጁነት እንዳለው ጠቁሟል።

መላው የከተማዋ ነዋሪ የፀጥታ ሀይሉ ባካሄዳቸው ዘመቻዎች ላይ እስከ አሁን ላደረገው ሁለንተናዊ ትብብርና ድጋፍ ኮሚሽኑ ምስጋና አቅርቧል።

በቀጣይም የፀጥታ ኃይሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርጋቸው ዘመቻዎች እንደ ወትሮው ከኮሚሽኑ ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.