Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማ ከ13 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ የሆነ ቦታ በህገ ወጥ መንገድ ተወሯል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 121 ወረዳዎች 13 ሚሊየን 523 ሺህ 634 ካሬ ሜትር ቦታ በህገ ወጥ መንገድ መወረሩ ተጠቆመ።

የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ‘የመሬት ቀበኞች’ በሚል ባዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም እንዳመለከተው፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ቀዝቀዝ ብሎ የነበረው የመሬት ወረራ እንደ አዲስ አገርሽቶ እየተስፋፋ መጥቷል።

ህገ ወጥነቱ በሁሉም ክፍለ ከተማ ያለ ሲሆን ችግሩ በስፋት የሚታይባቸው ቦሌ፣ የካ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲና ጉለሌ እንደሆኑም ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተደረገ ጥናት እንደተረጋገጠው በ121 ወረዳዎች 13 ሚሊየን 523 ሺህ 634 ካሬ ሜትር ቦታ በህገ ወጥ መንገድ ተወርሯል።

በድርጊቱ የሪል ስቴት አልሚዎችና የሃይማኖት ተቋማት በዋናነት እንደተሳተፉም ተጠቁሟል።

በሪል ስቴት አልሚዎች 184 ሺህ 208 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ደግሞ ከ97 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የሆነ ቦታ በህገወጥ መንገድ ተይዟል።

በህገ ወጥ መንገድ በተመሰረቱ 64 መንደሮች 6 ነጥብ 8 ሚሊየን ካሬ ሜትር ቦታ የተወረረ ሲሆን 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ መሬት በህገ ወጥ መንገድ ታጥሮ መገኘቱን አመላክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚህ መጠን ችግሩ መስፋፋቱ የመሬት ወረራ የቆየ፣ የከረመና ስር የሰደደ ችግር መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

መሬት ወረራ ላይ የሚሳተፈው አካል ብዙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩ በዋናነት የሚጀምረው ከመንግስት ተቋም እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

“የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ደላሎች፣ ባለሃብቶች፣ እንዲሁም የእምነት ተቋማት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጭምር” በማለት የህገወጥ ድርጊቱ ተሳታፊዎች በርካታ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የመሬት ወረራ በስፋት የተካሄደባቸው ወቅቶች መንግስት በተለያየ ምክንያት ውጥረት ውስጥ የገባበት ጊዜ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዋ፤ ሁከት፣ ምርጫና ሌላ መንግስት ጫና የገባበት ጊዜ ሰፋ ያለ የመሬት ወረራ እንደተካሄደበት አንስተዋል።

በዚህ አጋጣሚ መሬትን በመውረር ብዙዎች ትልልቅ ሃብት ማፍራታቸውን የጥናት ግኝት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

በአቋራጭ ሃብት አግኝቶ መሬትን እያገላበጡ መሸጥ ትልቅ ችግር መሆኑን ገልጸው፤ “መሬት እየለማ ከሆነ ችግር አይደለም” ብለዋል።

የመሬት ወረራ ሲፈጸም ህዝቡ ህገ ወጥነት እንዲስፋፋ ሽፋን ከመስጠት መጠንቀቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

“በተለይ ከብሔርና ከማንነት ጋር ተያይዞ ሽፋን መስጠት ህገ ወጡ መደበቂያ እንዲያገኝ ማድረጊያ አንዱ ስልት ነው” ብለዋል ወይዘሮ አዳነች።

ህገወጥነትን ማጥፋትና ማስተካከል እንደሚቻል ጠቁመው፤ “ህገወጥነት እንዳያጠፋን መጠንቀቅ አለብን፤ ነዋሪው አሁን በጀመረው ደረጃ ያግዘን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.