Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ገበያን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ገበያን ለማረጋጋት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ እና ተጠሪ ተቋም የሆነው የህብረት ስራ ኤጀንሲ አመራሮች በጋራ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የተከሰተውን አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል በተለያዩ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት እያደረጉት ያለውን ተግባር የሚመሰገን መሆኑን ጠቅሰው፥ ህብረተሰቡ በብዛት የሚፈልጋቸው ምርቶች አቅርቦት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ማህበራቱ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት እና ሸቀጣ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና ቅልጥፍና በተሞላበት መንገድ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባም አንስተዋል።

የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ገበያን ለማረጋጋት ከክልሎች እና ከተለያዩ ፋብሪካዎች ጋር ትስስር በመፍጠር የተለያዩ ምርቶችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ እየሰሩ መሆኑን በመስክ ምልከታው ማረጋገጥ መቻሉ ተገልጿል።

በተለይም የዋጋ ንረት ታይቶባቸዋል በተባሉ ምርቶች ጤፍ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ሎሚ፣ ቲማቲም በርበሬና የተለያዩ የፋብሪካ ምርት የሆኑ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው መባሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.