Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እስካሁን ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ እስካሁን ከ300 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ላይ የኮሮና ቫይረስን ለመለየት ናሙና መወሰዱን ጤና ቢሮው አስታውቋል።

ቢሮው ናሙና ከሰጡት 300 ሺህ 547 ነዋሪዎች ውስጥ ከ17 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገልጿል።

ባለፉት 24 ሰዓታትም ለ4 ሺህ 773 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በ601 ሰዎች ላይ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውም ነው የገለጸው።

ጤና ቢሮው እስካሁን ቫይረሱ በክፍለ ከተማ ደረጃ ያለበትን ሁኔታም በቅደም ተከተል ይፋ አድርጓል።

በዚህ መሠረት ቫይረሱ ቦሌ ክፍለ ከተማ 2 ሺህ 551፣ ጉለሌ 2 ሺህ 145፣ አዲስ ከተማ 1 ሺህ 878፣ አራዳ 1 ሺህ 736፣ የካ 1 ሺህ 684፣ ኮልፌ ቀራኒዮ 1 ሺህ 563፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ 1 ሺህ 421፣ ቂርቆስ 1 ሺህ 409፣ ልደታ 1 ሺህ 369 እንዲሁም አቃቂ 988 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

በተጨማሪም አስገድዶ ማቆያ ውስጥ ያሉ 320 እና አድራሻቸው ያልታወቁ 271 ሰዎች ላይም ቫይረሱ መገኘቱን ያስታወቀው ጤና ቢሮው፤ በአዲስ አበባ እስካሁን ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 17 ሺህ 335 መድረሱንም አመላክቷል።

ባለፉት 24 ሰዓታት በቫይረሱ ከአዲስ አበባ ብቻ 14 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉንም ቢሮው ማስታወቁን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 26 ሺህ 204 የደረሰ ሲሆን የ479 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.