Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መበራከቱን ተከትሎ ምርመራው በስፋት እየተካሄደ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአዲስ አበባ በኅብረተሰቡ ውስጥ መሰራጨቱ በመረጋገጡ የምርመራ አድማሱን በማስፋት በተለይም በሥራቸው ባህሪይ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች ላይ ምርመራው ተጠናክሯል።

በተለይም የቫይረሱ ስርጭት በስፋት በተስተዋለባቸው የአዲስ አበባ ልደታና አዲስ ከተማ ከፍለ ከተሞችና አካባቢዎች የምርመራ ስራው እየሰፋ መሆኑን ነው ዶክተር ሊያ የተናገሩት።

በከተማዋ የሚደረውን እንቅስቃሴ መዝጋት ሁነኛ መፍትሄ አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ ቫይረሱን ለመከላከል የሚወጡ መመሪያዎችን መተግበር ከተቻለ ስርጭቱን መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

በተጓዳኝም ቫይረሱ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለበትን ደረጃ ማወቅ የሚያስችል የአንቲ ቦዲ ቴስት ወይም ከደም ናሙና በመውሰድ የመመርመር ሥራ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።

የምርመራ ሥራውን በአዲስ አበባ ሳይወሰን በክልሎችም የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የሚካሄድባቸው ማዕከላት ቁጥር 29 መድረሱንና ለእነዚህም 32 የመመርመሪያ መሳሪያዎች መገጠማቸውን ገልጸዋል።

ማዕከላቱ በሙሉ አቅማቸው መሥራት ከቻሉ በቀን እስከ 7 ሺህ 500 ሰዎችን መመርመር እንደሚችሉ ጠቁመው አሁን ላይ በቀን እስከ 5 ሺህ ሰው አየመረመሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጓዳኝ የመመርመሪያ ኪቶችን በግዥና በልገሳ ለማሰባሰብ ጥረቶች አየተደረጉ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠዋል።

ለቫይረሱ ህሙማን የሚያገለግሉና በአገር አቀፍ ደረጃ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ የጽኑ ህሙማን የመተንፈሻ አካል ድጋፍ መሣሪያዎችን የማስፋት ሥራ መሰራቱንም ዶክተር ሊያ ጠቁመዋል።

ቫይረሱ በአገሪቱ በተከሰተ ጊዜ የነበሩት የጽኑ ህሙማን የመተንፈሻ አካል ድጋፍ መሣሪያዎች በቁጥር 22 እንደነበር አስታውሰው አሁን 221 መድረሱን ተናግረዋል።

ቁጥሩን ማሳደግ የተቻለው በግዥና ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ መሣሪያዎችን በመጠገንና ወደ ሥራ በማስገባት መሆኑንም አብራርተው ፤በአገር አቀፍ ደረጃ 3 ሺህ 600 ኦክስጅኖችም ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ኦክስጅን የሚያመርቱ ተቋማት ምርቱን በስፋት እንዲያቀርቡ ለማስቻል ድጋፍ ማድረጉንም አክለዋል።

ዶክተር ሊያ ኅብረተሰቡ በመንግሥትና በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎችን በመተግበር እያደረገ ያለውን ጥንቃቄ እንዲቀጥልም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.