Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የኮቪድ-19 ሕሙማንን ለሚያክሙ 1 ሺህ 750 የጤና ባለሞያዎች ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶች ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የኮቪድ-19 ሕሙማንን እያገለገሉ ለሚገኙ 1 ሺህ 750 የጤና ባለሙያዎች ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶች መዘጋጀታቸውን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደስ ገልጸዋል።

የኮቪድ ሕሙማንን የሚያክሙ የጤና ባለሞያዎች ራሳቸውን ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳያደርጉ የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁስ በማቅረብ ረገድ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በሁሉም ክልሎች ጊዜያዊ መኖሪያዎችን ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጤና ባለሞያዎች ባልታወቀ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ቢፈጠር ተለይተው የሚቆዩበት እና በበሽታው ቢያዙ የሚታከሙበት ቦታ መዘጋጀቱንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ተከትሎ ለጤና ባለሞያዎቹ እነዚህ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የጤና ባለሞያዎቹ መቼ እና በምን መልኩ ወደ ለይቶ ማቆያ መግባት እንዳለባቸው የሚያመላክቱ መመሪያዎች ከጤና ባለሞያዎች እና ከዘርፉ ማኅበራት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለጤና ባለሞያዎች እና ሠራተኞች የሚቀርቡ የኢንፌክሽን ቁሳቁስ እና አልባሳት በግዥ፣ በዕርዳታ እና በማምረት የማሟላት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለጤና ባለሞያዎች የሚቀርቡ ደረጃቸውን የጠበቁ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሕክምና የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች መከፋፈላቸውንም መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በመጪዎቹ ሳምንታትም በልገሳ እና በግዥ 25 ሚሊየን የፊት ጭምብሎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለሕክምና ባለሞያዎች እንደሚሰራጩም አመልክተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የፊት ጭምብሎች እጥረት ስላለ የጤና ባለሞያዎች ይህን ከግምት በማስገባት በጥንቃቄ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.