Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማዋ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ትምህርትን በመደበኛ መልኩ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ቢሮው ገልጿል።

ከነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የመዘገቡ ሲሆን፤ በመንግሰት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከመስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን የመመዝገብ ስራ እያከናወኑ ይገኛል።

የከተማው ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዳኞው ገብሩ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን በመግለፅ ተማሪዎች ጤንነታቸው ተጠብቆ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉም ከወላጆች፤ መምህራንና ርዕስ መምህራን ጋር ውይይት እንደሚደረግ ገልፀዋል።

የኮሮና ቫይረስ መከሰት ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደረባቸው ዘርፎች የሚጠቀሰው የትምህርት ዘርፉ ፤ ቫይረሱን በመካላከል ተማሪዎች ከትምህርታቸው ርቀው እንዳይቆዩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ትምህርት የሚያገኙበትና የተለያዩ ምዘናዎች የሚሰሩበት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም ምንም እንኳ ሁሉም ወደ ተግባር ገብቷል ባይባልም ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይርቁ ያስቻለ መሆኑም ተጠቅሷል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ እንደተናገሩት በተደረገው ጥረት የተማሪዎች አዕምሮ ከእውቀት እንዳይርቅ አግዟል፡፡

ቀደም ሲል በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የቅኝት ስራ በማከናወን ምን ያህል የመማሪያ ክፍል እና የተማሪዎች መገልገያ ቁሳቁስ እንዳለ ጥናት መደረጉን ምክትል የቢሮ ሃላፊው ገልጸዋል።

ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት የጸረ-ቫይረስ ኬሚካል ርጭት እንዲካሄድ ይደረጋል ያሉ ሲሆን ከጤና ባለሙያዎች ጋርም በቅርበት እየሰሩ እንደሆነም ነው ምክትል የቢሮ ሀላፊ ከፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ የገለጹት።

አሁን በመዲናዋ ትምህርትን ለማስጀመር የተደረገው ዝግጅት የተሻለ ነው የሚሉት ምክትል ሃላፊው መንግሰት በሀገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት ይጀመር ሲባል ለመጀመር ቅደመ ሁኔታዎች ተጠናቀዋል።

በሲሳይ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.