Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አባባ ከተማ የተፈጠረውን የቀይ ሽንኩርት፣ የጤፍና ዘይት እጥረት ለመቅረፍ እየተሰራነው

አዲስ አበባ፣ግንቦት 20፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አባባ ከተማ የተፈጠረውን የቀይ ሽንኩርት፣ የጤፍና የዘይት እጥረት ለመቅረፍ እየተሰራመሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊው አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ከፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በአሁን ወቅት በመዲናዋ ቀደም ሲል ከውጭ የሚገባ የሽንኩርት ምርት በተለያዩ ምክንያት አቅርቦት እየተስተጓጎለ መሆኑን ተከትሎ በቀይ ሸንኩርት ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል ብለዋል።

ከዋጋ ቁጥጥሩ በተጨማሪ ከሽንኩርት አምራች አካባቢዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የሽንኩርት አቅርቦት በማጠናከር የዋጋ ጭማሪውን የማስተካከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ከጤፍ ጋር ተያይዞ አቅርቦቱን በማሻሻል ከተለያዩ ክልሎች ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሌላም በኩል የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ፣ ምርት የደበቁና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ ከ767 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን ቢሮው አስታውቋል።

የንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በአንድንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማገርሸት መጀመሩን ጠቁመው፥ ከቁጥጥሩ ባሻገር በበቂ ደረጃ ምርቶቹን የማቀረብ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ምርት የማከማቸትና የመደበቅ እና በምርቶች ላይ ከፍተኛ ዋጋ የመጨመር፣ በተለያዩ ምርቶች የዋጋ ንረትና ሰው ሰራሽ እጥረት በሚያስከትሉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃው እንደቀጠለ ገልጸዋል።

ከዚያም ባለፈ የምርቶች ዋጋ ባለበት እንዲቆይ ለማድረግ እና የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የአቅርቦት ማሻሻልና ትስስር መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ በመስራት ላይ መሆናቸውን የቢሮ ሃላፊው አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ተናገረዋል።

ከዚያም ባለፈ በትናንትናው እለት ከ10ሩም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ ዩኒየኖች አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይት የዋጋ ጭማሪ በታየባቸው ምርቶች ላይ ቅድሚያ ሰጥተው አቅርቦቱን እንዲያሻሽሉ አቅጣጫ መቀመጡን ሃላፊው ገልጸዋል ።

የአዲስ አባባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ በበኩሉ በተለያዩ አማራጮች የተለያዩ ምርቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ እያደረኩነው ብሏል።

ኤጀንሲው በመዲናዋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ካሳለፍነው መጋቢው ወር ጀምሮ 56 ሺህ 495 በላይ ኩንታል ጤፍ ፣ የስንዴ እና ጥራጥሬዎችን ከተለያዩ ክልሎች በማስገባት ለሸማቹ ማሰራጨት መቻሉን ገልጿል።

ይሁንና በአሁን ወቅት በቀይ ሸንኩርት፣ በጤፍና በዘይት በኩል እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪን ለመቀነስ እና ገበያውን ለማረጋጋት በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ዩኔኖች ጋር እየተሰራ ነው ያሉት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ የምርት እጥረት የለም ይላሉ።

በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ጤፍ በወፍጮ ቤት ደረጃ በኩንታል 3 ሺህ 800 ብር በላይ እንዳይሸጥ ዘይትም በነጋዴው ባለ አምስት ሊትር 380 ብር በላይ እንዳይሸጥ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ይሁንና ህብረተሰቡም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉና ምርት የሚደብቁ ነጋዴዎችን ጥቆማ በመስጠት ተጠያቂ ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.