Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመጋዘን ግንብ ተደርምሶ በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት አደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአንድ መጋዘን ግንብ ተደርምሶ በሰው ህይወትና አካል እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

አደጋው የደረሰው ዛሬ በግምት ከቀኑ 9:30 ሰዓት ሲሆን ፥ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ክልል ልዩ ቦታው አማኑኤል ሆስፒታል አካባቢ ነው።

በመጋዘን ቤት ውስጥ ውሃ በመሙላቱ ግንቡ ተደርምሶ ከስር በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በነበሩ 3 ግለሰቦች ላይ ጉዳት በማድረስ የ1ሰው ህይወት ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ሲያልፍ ፤ 2 ግለሰቦች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የመሳለሚያ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የዕለቱ ተረኛ መኮንን ምክትል ኮማንደር መዓዛ ገብረማርያም ገልፀዋል።

ኮማንደሯ አክለውም ፥ በአፋጣኝ አደጋው በደረሰበት ቦታ በመሄድ ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የማውጣትና ወደ ህክምና እንዲሄዱ የማድረግ እንዲሁም ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ሰዎችን ከአደጋው ቦታ የማሸሽ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

አያይዘውም ፥ ከክረምቱ ወቅት ጋር ተያይዞ ለአደጋ ስጋት የሆኑ ቦታዎችን በመለየት የሚመለከታቸው አካላት ጉዳት ከመድረሱ በፊት ትኩረት በመስጠት የመፍትሔ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው መግለጻቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ፖሊስ በፍጥነት ቦታው ላይ ደርሶ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሰራውን ስራ አድንቀው ፤ ቀጣይም መጋዘኑ መፍትሔ ካልተበጀለት ስጋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.