Fana: At a Speed of Life!

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚታዩ ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት በፓርኩ ውጤታማነት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳሰበ፡፡
የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደርቤ ደበሌ ÷ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተቋቋሙበት ዓላማ የሥራ አጥ ችግርን ለመቅረፍ፣ የውጭ ምንዛሪን ለማስግኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማምጣት ቢሆንም ፓርኩ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ለቡድኑ አባላት አብራርተዋል፡፡
የውሃ እጥረት መኖሩ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩ በዘጠኝ ወር ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ በእቅድ ቢያዝም ግንባታው ከሦስት ዓመት በላይም አለመጠናቀቁ ይገኙበታል፡፡
ለአርሶ አደሮቹ ካሳ ያልተከፈለባቸው ቦታዎች ስላሉ ሥራ ተቋራጮቹ የግንባታ መሣሪያዎችንና መኪናዎችን ቢያስገቡም ከአንድ ዓመት በላይ መኪናዎቻቸውን አቁመው ሥራ አለመጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከዚያም ባለፈ የኢንዱስሪ ፓርኩን ለመገንባት ሲታሰብ የአርሶ አደሮቹን የመንገድ ችግር ያላካተተ ስለነበር እስካሁን ድረስ ሰዎችና እንስሳት በኢንዱስሪ ፓርኩ ውስጥ እንደሚመላለሱም ሥራ አስኪያጁ አክለው አስረድተዋል፡፡
የቡድኑ አባላት በበኩላቸው ÷ በምልከታ ወቅት ባስተዋሏቸው ጠንካራና ውስንነት ባለባቸው አፈጻጸሞች በሰጡት አስተያየት በኢንዱስትሪ ፓርኩ አካባቢ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ከፓርኩ የመብራትና የውሃ አገልግሎቶች እንዲያገኙ ቢደረግና በፓርኩ ዙሪያ ያሉ ሥራ አጥ ወጣቶችንም በማሳተፍ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በትኩረት መሰራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የቡድኑ አስተባባሪ አቶ አብዱላሂ ሀሙ በኢንዱስትሪ ፓርኩ የአንድ መስኮት አገልግሎት መሰጠቱ፣ ፓርኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ከወረቀት ነፃ መሆኑ፣ በፓርኩ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር መፈታቱ፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚሰሩ ሠራተኞች እንዳይቀነሱ መደረጉና ሼዶቹ በክፍት ቦታ ተተክለው አገልግሎት መስጠታቸውን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡
በአንፃሩ ኪክደምና ሰንሻይን ኮንስትራክሽኖች እስካሁን ወደ ሥራ አለመግባታቸውን፣ ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ጥበቃ ባለመመደቡ ለስርቆት መዳረጉንና አጥር ባለመኖሩም ፓርኩ የእንስሳት መናኸሪያ መሆኑን በእጥረት ገምግመዋል፡፡
አክለውም የኢንዱስትሪ ፓርኩ የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች በአግባቡ ካልተሰሩ ፓርኩን ሊያጥለቀልቁ እና አካባቢውን ሊበክሉ ስለሚችሉ በጥንቃቄ መሰራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የፓርኩ አመራሮች ካሳ የተፈለበት የፓርኩ ክልለ ላይ ሕዝቡ መልሶ የሰፈረበትን ምክንያት መጠናት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮቹን መቅረፍ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም የቡድኑ አስተባባሪ አቶ አብዱላሂ ሀሙ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉት ችግሮች ተቀርፈው ፓርኩ ውጤታማ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴውም የመፍትሄው አካል ለመሆን በዝርዝር የተጠቀሱ ችግሮችን ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሪፖርት እንደሚያደርግ እና ለኢንዱስትሪ ፓርኩም ዝርዝር ግብረ መልስ በጽሑፍ እንደሚልክ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.