Fana: At a Speed of Life!

በአዳማ ከተማ የምርጫ ሂደቱን ለማወክ በመሞከርና በምርጫ ጣቢያ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት የተከሰሱ ተቀጡ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ ከተማ የምርጫ ሂደቱን ለማወክ በመሞከርና በምርጫ ጣቢያ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ጋልሜቻ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ ግለሰቦቹ ሰላማዊውን የምርጫ ሂደት ለማወክ በመሞከርና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ስንታየሁ ዑርግዬ የተባለ ግለሰብ በአዳማ ከተማ አባገዳ ክፍለ ከተማ ኦዳ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘቱ በአዋጅ ቁጥር 1177/2011 ዓ.ም የተቀመጠን ክለከላ በመጣስ ወንጀል ተከሶ መቀጣቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በዚሁ ክፍለ ከተማ በምርጫ ጣቢያ ስድስት ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ40 ላይ ከማል አብዶ የሚባል ግለሰብ ድምፅ ሰጪ መስሎ ድምፅ መስጫ ጣቢያው ድረስ በመግባት ሂደቱን ለማወክ ጥረት በማድረጉ መቀጣቱን አመልክተዋል።

በምርጫ ወቅት ሊኖሩ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመመልከት የተቋቋመው የአዳማ ወረዳ የወቅታዊ ጉዳይ ችሎት ግለሰቦቹ በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቀዋል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ የተገኘው ስንታየሁ ዑርግዬ በአንድ ዓመት እስራትና በ5 ሺህ ብር መቀጣቱን ተናግረዋል።

ምርጫውን ለማስተጓጎል የሞከረው ከማል አብዶ የተባለ ግለሰብ ደግሞ በስምንት ወር እስራት መቀጣቱን ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.