Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ለተሰማሩ የሕንድና ባንግላዴሽ ባለሀብቶች በትግራይ ክልል እየተወሰደ ስላለው ህግ የማስከበር እርምጃ ገለጻ ተደርጓል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ የሕንድና የባንግላዴሽ ባለሀብቶች በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ማብራሪያ መሰጠቱን በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ትዝታ ሙሉጌታ ገለጹ።

የሕወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሃገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

አምባሳደሯም ለባለሃብቶቹ እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ ዙሪያ ማብራሪያና ገለጻ ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በግብርና፣ የአበባ እርሻ ልማት፣ መድሐኒት ማምረቻ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የሕንድ ኩባንያዎች በዋነኝነት በኢትዮጵያ የተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ናቸው።

ኢትዮጵያና ባንግላዴሽም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ትብብር እያደገ የመጣ ሲሆን፤ የባንግላዴሽ ኩባንያዎች በዋናነት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስኮች በኢትዮጵያ ተሰማርተዋል።

ከኩባንያዎቹ አንዱ ዲቢኤል ግሩፕ ሲሆን በ2010 ዓ.ም ተመርቆ በተከፈተው የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ ሲሆን ምርቶቹን ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይልካል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.