Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በቴሌኮም ኦፕሬተርነት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተጫራቾች የሚያወያይ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን ለመምረጥ የሚያስችልና በቴሌኮም ኦፕሬተርነት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተጫራቾችን የሚያወያይ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ዛሬ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አዘጋጅነት ተካሂዷል፡፡

የቪዲዮ ኮንፈረንሱ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ፍላጎት ያላቸው ተጫራቾች በሂደቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄዎች ለመመለስና በሂደቱ ለመሳተፍ የሚያስፈልጓቸውን መረጃዎች ለመስጠት ታቅዶ የተዘጋጀ  መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ÷ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ወደ ገበያ እንዲገቡ የማድረጉ ጥረት ጤነኛ የገበያ ውድድር በመፍጠር የተሻለ የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት ከማስቻሉም በላይ ተደራሽነትን በማስፋት በመንግሥት የተቀመጠውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግብ የሚያሳካም እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከብሄራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከኢትዮ ቴሌኮም የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን÷ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ከቴሌኮም አገልግሎት ጋር በተዛመደ ከመስሪያ ቤታቸው ተግባርና ሀላፊነት አንጻር ፍላጎት ላላቸው ተሳታፊዎች አስፈላጊውን መረጃ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ላይ በቴሌኮም ኦፕሬተርነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቁ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን÷ ድርጅቶቹ ላነሷቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ጉዳዩ በሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ማብራሪያና ወቅታዊ መረጃ እንደተሰጣቸው ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.