Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ተጨማሪ 2 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 286 ግለሰቦች መካከል ነው ሁለቱ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠው ብለዋል የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ።

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 71 ደርሷል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳስታወቁት፥ ዛሬ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁለቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሁለቱም ሴቶች ሲሆኑ፥ አንዷ የ24 ዓመት እድሜ ያላትና ከአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውሳኔ በፊት ከዱባይ የተመለሰች መሆኗን መግለጫው አመላክቷል።

ሌላኛዋ ግለሰብ የ35 ዓመት እድሜ ያላትና ከቱርክ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ክትትል ስታደርግ የነበረች ናት።

እስካሁን ባለው ሂደት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለ3 ሺህ 863 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ መከናወኑም በመግለጫው ተጠቁሟል።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ግለሰቦች መካከል 56ቱ የህክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።

አሁን ላይ በጽኑ ህሙማን ክፍል ክትትል የሚደረግላቸው ህሙማን አለመኖራቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።

ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋጋጠባቸው ግለሰቦች መካከል ሶስት ሰዎች በቫይረሱ ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.