Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ተጨማሪ 3 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተገለጸ

በኢትዮጵያ ተጨማሪ 3 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፥ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ያለበት የመጀመሪያው ሰው ከተገኘ በኋላ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ሲከታተል መቆየቱን አስታውቋል።

በዚህ መሰረትም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው 117 ሰዎች ተለይተው የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ቫይረሱን ለመለየት የሚያስችል ምርመራ ለማድረግ ከግለሰቦቹ ናሙና እየተወሰደ መሆኑ ተመላክቷል።

ምርመራ ከተደረገላቸው እና ከመጀመሪያው ተጠቂ ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ ከነበራቸው ሰዎች መካከልም ሶስት ግለሰቦች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥም ሁለቱ የ44 እና የ47 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የጃፓን ዜጎች ሲሆን፥ አንደኛው ደግሞ የ42 ዓመት ኢትዮጵያዊ መሆኑ ታውቋል።

ሶስቱም ግለሰቦች በአዲስ አበባ ውስጥ የሚሰሩ እና ቫይረሱ ከተገኘበት የመጀመሪያው ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው መሆኑን የገለጸው ኢንስቲትዩቱ፥ ከተጠቂዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች የማፈላለጉ ስራ መጀመሩንም ጠቁሟል።።

በአሁኑ ስዓት የመጀመሪያው ታማሚ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የህክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑ ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና ከሳዑዲ ዓረቢያ የመጣ ግለሰብ የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች ያሳይ ስለነበር ወደ ለይቶ ማቆያ በመወሰድ ላይ እያለ የሚጓጓዝበትን አንቡላንስ መኪና መስኮት በመስበር አምልጦ እንደነበር ተገልጿል።

ይሁን እንጂ ኢንስቲትዩቱ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ክትትል ግለሰቡ በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅትም ከግለሰቡ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.