Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ አራት የዘይት ፋብሪካዎች የሙከራ ምርት ጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 4 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ አራት የዘይት ፋብሪካዎች የሙከራ ምርት ማምረት መጀመራቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ በመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ እየተገነቡ ካሉት ግዙፍ 17 የዘይት ፋብሪካዎች አራቱ (ቡሬ፣ ደብረ ማርቆስ፣ አዳማና ድሬዳዋ ዘይት ፋብሪካዎች) በያዝነው ወር ለገበያ የሚቀርብ ዘይት ወደ ማምረት ይገባሉ።

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባውን የዘይት ምርት በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች የመተካት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ለዘርፉ ባለሀብቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍና እገዛ በማድረግ በዚህ አመት የሀገሪቱን የዘይት አቅርቦት እንዲሸፍኑ በማድረግ ከውጭ የሚገባውን ዘይት የማስቆም ግብም ተቀምጧልም ነው ያሉት።

የዘይት አቅርቦትን በሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች መተካት መቻሉ ለህብረተሰቡ ክፍል ተስፋን እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም ለፋብሪካዎቹ የግብአት አቅርቦትን ለማመቻቸት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች የአኩሪ አተር ምርት ለማቅረብ ባለሀብቶች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

የሀይል አቅርቦት እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎችም ለፋብሪካዎቹ ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራቱንም አስረድተዋል፡፡

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.