Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ አንድ የ9 ወር ህጻንን ጨምሮ ተጨማሪ 8 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 264 ሰዎች ውስጥ 8 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው።
 
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል አንድ የዘጠኝ ወር ህጻን የሚገኝ ሲሆን፥ እናቱም ቫይረሱ ተገኝቶባታል።
 
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት በ24 ሰዓታት ውስጥ ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች መካካል አንዱ ኤርትራዊ ሲሆን ቀሪዎቹ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።
 
ይህም በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎችን ቁጥር 52 አድርሶታል ነው ያሉት።
 
በሽታው እንደሚገኝባቸው ከተረጋገጠ 8 ሰዎች መካከል አምስቱ ከዱባይ የመጡና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩ ናቸው።
 
ከእነዚህም ውስጥ አንድ የዘጠኝ ወር ህጻንና ወላጅ እናቱ ይገኙበታል።
 
አንድ የ25 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊት ከታይላንድ መጥታ በለይቶ ማቆያ ክትትል ስታደርግ የነበረች ሲሆን፥ አንድ የ19 ዓመት ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ጉዞ ታሪክ የሌለው ሲሆን የንክኪ ሁኔታውም በመጣራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
 
ወጣቱ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ንክኪ እንዳለው ተጠርጥሮ በለይቶ ማቆያ የነበረ ነው።
 
ሌላኛዋ የ30 ዓመት ሴት ኤርትራዊት ስትሆን ከእንግሊዝ ለንደን መጥታ በአዲስ አበባ በለይቶ ማቆያ ክትትል እያደረገች የምትገኝ ናት።
 
በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች የኮሮናቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ አቅም እየጨመረ መጣቱንም ገልጸዋል።
 
በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ይገኛሉ።
 
አራቱ ያገገሙ ሲሆን፤ ሁለቱ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.