Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የባለሙሉ ፕሮፌሰሮች ካውንስል ተመሰረተ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የባለሙሉ ፕሮፌሰሮች ካውንስል ተመሰረተ።

የካውንስሉ ምስረታ ምሁራን ከሚኒስቴሩ ጋር በመቀናጀት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ግቦችን ለማሳካትና በሃገር ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ ለመፍጠር ያለመ ነው።

ምሁራኑ ለሃገራቸው ብልጽግና በዕውቀታቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ካውንስሉ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ይደራጃል ተብሏል።

ካውንስሉ የመምህራንና የአሰልጣኞች ልማት፣ የትምህርትና ስልጠና ጥራትና አግባብነት፣ የምርምር ጥራት አግባብነትና ተደራሽነትን ጨምሮ ሰባት የትኩረት መስኮች እንዳሉትም ተገልጿል።

በተጨማሪም የአካዳሚክ፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዓለም አቀፍ ሃብት ማፈላለግ ጉዳዮችን የሚያካትቱ አምስት ቋሚ ኮሚቴዎችን አደራጅቶ ሥራውን ይከውናል ነው የተባለው።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ ካውንስሉ የተቋቋመው ኢትዮጵያውያን ምሁራን ለሃገራቸው ልማት የዕውቀት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማሰብ መሆኑን ገልፀዋል።

ምሁራኑ በሃገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያው ትኩረት በተደረገባቸው ማዕድን፣ ግብርና፣ ቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ምሁራኑ በመምህራንና አሰልጣኞች ልማት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ካውንስሉ የበላይ ጠባቂ የሚኖረው ሲሆን ተጠሪነቱ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይሆናል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ፣ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር የሚያገለግሉ፣ በምርምር ተቋማት የሚሰሩና በጡረታ ላይ ያሉ ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች በፈቃደኝነት የካውንስሉ አባል መሆን ይችላሉም ተብሏል።

በጉባዔው ከ170 በላይ ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሃገራት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያ በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጤና፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች የሚሰሩ 236 ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች እንዳሏት ሚኒስቴሩን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.