Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በመጪው ጳጉሜን ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ከጳጉሜን 2 እስከ 4 ቀን 2014 በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

ጆርካ ኤቨንትስና ኤቲኤክ በጋራ የሚያዘጋጁት ይህ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ÷ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ፣ የእስያና የሰሜን አሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ይሳተፉበታል ተብሏል።

አውደ ርዕዩን አስመልክቶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲና የጆርካ ኤቨንትስ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳምሶን ኃይለእየሱስ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ላይ ምርትና አገልግሎቶችን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ዙሪያ አፍሪካንና ሌላውን ዓለም ለማስተዋወቅ ይረዳል ነው የተባለው፡፡

አውደ ርዕዩ ለኢትዮጵያ በርካታ ጥቅም ያመጣል ያሉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ÷ በዋናነት በሀገር ገፅታና በኢኮኖሚ ግንባታ ላይ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማሳደግና ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን ወደሀገር ለማምጣት እንደሚረዳ ጠቅሰው÷ የተሳካ እንዲሆን የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በሶላር ቴክኖሎጂ፣ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፣ በዲጂታል የክፍያ ስርዓቶች እንዲሁም በቴሌኮሙኒኬሽን እና በባንክ ስራዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጆርካ ኤቨንትስ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳምሶን ኃይለእየሱስ ናቸው።

ከ45 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እንደሚሳተፉበት የታመነበት ይህ አውደ ርዕይ፥ በቴሌኮም ዘርፍ፣ በሳይበር ደህንነት፣ በባንክና ኢንሹራንስ፣ በባዮ ቴክኖሎጂና በሶላር ቴክኖሎጂ ዘርፎችና በሌሎችም በርካታ ለሀገር ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች ላይ የውጭ ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሏል።

በዓለምሰገድ አሳዬ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.