Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የኮምፒውተር ወንጀል እንዴት ይታያል?

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮምፒዩተር ወንጀልን መደበኛ ከሆኑ ወንጀሎች ለየት የሚያደርጉት ሶሰት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉት፡፡

አነዚህ ሶሰት መሠረታዊ ጉዳዮች በቴክኖሎጂ እና እዉቀት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣ መጠነ ሰፊ ሉላዊነት ያለው /ድንበር የለሽ/ መሆኑ እንዲሁም በሳይበር ምህዳር ላይ የሚፈፀመው የወንጀል አይነት አዲስና ኢ-ተገማች መሆን ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ይህን ወንጀል ለመቆጣጠር ያስችል ዘንድ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ 958/2008 ስራ ላይ ያዋለች ሲሆን፥ በአዋጁ የተካተቱት የወንጀል አይነቶች በሶስት ዘርፍ ይቀመጣሉ፡፡

እነዚህም ኮምፒዩተር እና የኮምፒዩተር ሥርዓትን ኢላማ ያደረጉ ወንጀሎች፥ በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካኝነት የሚፈፀም ወንጀል እና ስለህገ-ወጥ የይዘት ዳታ ናቸው፡፡

እነዚህን የወንጀል ተግባራት ለመቆጣጠር ያስችል ዘንድ በአዋጁ የገንዘብ እና የእስራት ቅጣት የተደነገገ ሲሆን፥ የወንጀሎቹ ደረጃና የቅጣት መጠን በአምስት ደረጃዎች ተከፍለዋል፡፡

እነዚህም ወንጀሉ ግለሰብ ላይ ሲያነጣጥር፥ ህጋዊ የሰውነት አካላት ላይ ሲያነጣጥር፥ ቁልፍ ተቋማት ላይ ሲያነጣጥር፥ ጥብቅ ምስጢር ተብሎ በተሰየመ የኮምፒዩተር ዳታ፣ ሥርዓት ወይም ኔትዎርክ ላይ ሲያነጣጥር ወይም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወይም ሀገሪቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ በምትገኝበት ወቅት ከተፈጸመ ነው፡፡

የህብረተሰቡ የኮምፒውተር አጠቃቀም ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ አዋጁ ሆን ተብለው በሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአዋጁ የተቀመጠዉ የቅጣት መጠንም ከ5ሺህ እስከ 500ሺህ ብር እና ከአንድ ዓመት ከማይበልጥ ቀላል እስራት ጀምሮ እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ድንጋጌ አካቷል፡፡

አዋጁ የኮምፒውተር ወንጀል መከላከል የሚያስችሉ መሰረታዊ እና የስነ-ስርዓት ህጎችን ያካተተ ነዉ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.