Fana: At a Speed of Life!

በኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የተመራ ልዑክ የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ ሂደትን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የተመራ የፌዴራል እና የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች ልዑክ የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ ሂደትን ጎብኝቷል፡፡

ልዑኩ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የሚገኘውን የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ ሂደትን ነው ተዘዋውሮ የተመለከተው፡፡

የግንባታ ሂደቱ ከተጀመረ 19 ወራትን ያስቆጠረው የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ÷ ሦስት የግንባታ ምዕራፎች አሉት ተብሏል።

በመጀመሪያው ዙር የግንባታ ምዕራፍ በቀን 9 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ማምረት የሚችለው ግንባታ በ340 ሚሊየን ብር ወጪ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ባለፉት ወራት የግንባታ ሂደት የመንገድ እና የውኃ መሠረተ ልማቶች በባለሃብቶቹ የተሟሉለት ፕሮጀክቱ የአሥተዳደር ቢሮዎች እና ንብረት ክፍል ግንባታ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ገብቷል።

እንደ አሚኮ ዘገባ÷ 2 ሺህ ሠራተኞችን የሚይዝ መጠለያ ግንባታም በሂደት ላይ ነው ተብሏል።

በጉብኝት መርኃግብሩ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል ተመሥገን ጥሩነህ፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌውን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.