Fana: At a Speed of Life!

በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ድርጊቶች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ድርጊቶች በተቋሙ አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋ፥ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ድርጊቶችን ለመከላከል የተለያዩ አዋጆች በስራ ላይ የዋሉ ቢሆንም፥ የሚፈፀመው ውድመትና ስርቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል ነው ያሉት፡፡

ይህ ደግሞ በተቋሙ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅኖ እየፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ስርቆትና ውድመት ከሚደርስባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገዙ ግብዓቶች መሆናቸውን ጠቁመው፥ ይህ ደግሞ ተቋሙ ያስቀመጠውን ጥራት ያለውና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የመስጠት እቅድ እንዳይሳካ ዕንቅፋት እንደፈጠረ ጠቁመዋል፡፡

ከኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ስርቆት በተጨማሪ የኃይል ስርቆት የሚፈፅም ደንበኛ በኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 ዓ.ም መሰረት የህግ ተጠያቂ ይሆናል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በመሰረተ-ልማትና በኃይል ስርቆት 131 ወንጀሎች የተፈፀሙ መሆኑን የገለፁት አቶ አበበ ፥ በዚህም ምክንያት 16 ሚሊየን 283 ሺህ 400 ብር ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡

ህብረተሰቡ ሃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ አደጋ ሲያደረሱም ሆነ አጠራጣሪ ነገር ሲመለከት በአካባቢው ወደሚገኝ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ እንዲያሳውቅ፤ በአዲስ አበበ ከተማ ደግሞ በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በኩል ጥቆማ እንዲሰጥ ዳይሬክተሩ መጠየቃቸውን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.