Fana: At a Speed of Life!

በእጅ መፃፍ ማንበብን ለመማር የሚረዳ ውጤታማ ስልት እንደሆነ የጆን ሆፕኪንስ ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ዘመናዊነትን እና ስልጣኔን ተከትሎ ኮምፒውተር በአደጉ ሀገራትና በተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋ መምጣቱ ህፃናት ዝቅተኛ የንባብ ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረጉን የጆን ሆፕኪንስ ጥናት አመላክቷል፡፡ በጥናቱ ፊደላትን በእጅ መጻፍ የንባብ ክህሎትን ለማዳበር እንደሚያግዝ ተመላክቷል፡፡

እንደ ጥናቱ÷ አንድን ንድፈ ሀሳብ ወይም የትምህርት ይዘት በኮምፒውተር እየተየቡ ወይም በቪዲዮ እየተመለከቱ ከመማር ይልቅ በእስክርቢቶ ወይም በእርሳስ እየጻፉ መማር በሚያስደንቅ ሁኔታ የተሻለ መረዳትን እንደሚያስገኝ ተገልጧል፡፡

ይህም የጥናት ውጤት ወላጆችና አስተማሪዎች ህጻናት ብዙ ጊዜያቸውን በእርሳስና በወረቀት ላይ እንዲያሳልፉ እንዲያግዟቸው የሚያበረታታ ነው፡፡

የእጅ ጽሁፍ ውበትን ለማምጣት በተደጋጋሚ መለማመድ አንድ መፍትሔ ቢሆንም የእጅ ጽሁፍ ማማር ግን ብቻውን ትልቅ ስኬት እንዳልሆነ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ብሬንዳ ራፕ የእጅ ጽሁፍ ከአእምሮ እድገት ጋር የተያያዘ ጥቅም እንዳለውም በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡

በጥናቱ 42 ሰዎች የአረብኛ ፊደላትን ለሶስት ተከፍለው እንዲማሩ የተደረገ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ቡድን በእጅ በመጻፍ፣ ሁለተኛው ቡድን በኮምፒውተር በመጻፍ እና ሶስተኛው ቡድን ደግሞ በቪዲዮ በመመልከት ፊደላቱን ተምረዋል፡፡

በዚህም በእጅ ጽሁፍ ፊደላቱን ሲማሩ የነበሩት የጥናቱ ተሳታፊዎች በአጭር ጊዜ የአጻጻፍ ስርዓቱን መልመድ ችለዋል፡፡ የፊደል አጣጣል ስልቱንም በጥንቃቄ እና በትክክል ማስታወስ መቻላቸውን ነው የጥናቱ ውጤት ያመላከተው፡፡
በጽሁፍ ልምምድ ወቅት እጃችንና አእምሯችን በጋራ የሚያደርጉት ጥምረት የፊደላት ሁለንተናዊ ቅርጽ በአእምሯችን ላይ በቀላሉ እንዲሳል አድርጎታል፤ ይህም በንባብ ልምምድ ወቅት ፈጣን የአነባበብ አቅም እንዲኖር ያስችላል ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡

ምንጭ÷ ሜዲካልኤክስፕረስ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.