Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያና አፋር ክልሎች በ28 ሚሊየን ዶላር የሚተገበር የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች የሚገኙ ህጻናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር ይፋ ሆነ።

ለመርሃ ግብሩ 28 ሚሊየን ዶላር የተመደበ ሲሆን፥ 677 ሺህ 247 ህጻናት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

መርሃ ግብሩ በዓለም ምግብ ፕሮግራምና በአሜሪካ የግብርና ሚኒስቴር ትብብር ለአራት ዓመታት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ያሳቡ ብርቅነህ፥ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር በችግር ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ከትምህርት ውጪ እንዳይሆኑ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እያካሄደ ባለው የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር በፋይናንስ፣ በቴክኒክና በሌሎችም ሰፊ ልምድ የተገኘበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ሜቴክ ማጅ በበኩላቸው፥ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና አጋሮቹ በኢትዮጵያ መንግስት ለሚካሄደው የትምህርት ቤት ምገባ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አያይዘውም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከአሜሪካ የግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ላላፉት 10 አመታት ከ54 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ወደ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ህጻናትን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.