Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን የኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ንግድ ቢሮዎች ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አብዱላዚዝ ቃዶ በክልሉ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራ ኮሚቴ እስከ ወረዳ ድረስ በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የግብርና ምርቶችን ከሸማች ማህበራት እና ዩኒየኖች ጋር ትስስር የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አላስፈላጊ የንግድ ሰንሰለቶች ለማስወገድም ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ነው ያሉት::
ከዘይት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋትም በሀገር ውስጥ በሁለት ኩባንያዎች የተመረተ 4 ሚሊየን ሊትር ዘይት ለኦሮሚያ ክልሉ መመደቡን አንስተዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ ስርጭቱን ለማከናወንም ቢፍቱ አዱኛ አክሲዮን ማህበር ከተባለ የመንግስት ልማት ድርጅት ጋር ውል በመፈራረም የምርት ርክክብ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
እስካሁን በህገ ወጥ ነጋዴዎች ለይ በተወሰደ የቁጥጥር ስራም 4 ሚሊየን የሚጠጋ ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉን አውስተዋል፡፡

በደቡብ ክልል ንግድ ቢሮ የንግድ አሰራር እና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሃላፊ ተወካይ አቶ ኢሳያስ ሸዋኔህ በበኩላቸው ፤በክልሉ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በሁሉም የፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል፡፡

ችግሩም በምርት አቅርቦት ማነስ፣ በአላስፈላጊ የምርት ክምችት እና በህገ ወጥ ደላሎች ሳቢያ የተፈጠረ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡
ከዘይት ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው የዋጋ ጭማሪም መንግስት ያቀርበው የነበረው የዘይት ምርት መቆራረጥ እና በቅርቡ በሀገር ውስጥ የተመረተው ፊቤላ ዘይት በፍጥነት ባለ መሰራጨቱ የተከሰተ ነው ብለዋል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍም ዘይቱን ለማሰራጨት ፍቃድ ከተሰጠው ወንዶ ኩባንያ ጋር ስርጭቱን በፍጥነት እንዲያከናውን ስምምነት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ክልል የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት በሶስት ቡድኖች የተዋቀረ የባለሙያዎች ቡድን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መሰማራታቸውን አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የምርት ክምችት ያለባቸው እና ዕጥረት የተፈተረባቸው አካባቢዎች ተለይተዋል ያሉት ሃላፊው፣ በቀጣይም በህብረት ስራ ማህበራት ውስጥ የሚገኙ መሰረታዊ የፍጃታ እቃዎችን እና የግብርና ምርቶችን እጥረት ወደ ተከሰተባቸው ቦታዎች የማሰራጨት ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
መንግስት በሚያደርገው ቁጥጥር ብቻ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር አይቻልም ያሉት የቢሮ ሃላፊዎቹ ፣ ማህበረሰቡም ህገ ወጥ የዋጋጭ ማሪ ሲመለከት ለሚመለከታቸው አካላት በመጠቆም የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.