Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በኮቪድ-19 የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ለማነቃቃት ያለመ የመስህብ ስፍራዎች ጉብኝት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በኮሮና ቫይረስ) ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ለማነቃቃት ያለመ የመስህብ ስፍራዎች ጉብኝት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ነው።

መነሻውን ላንጋኖ ሀይቅ፤ መዳረሻው ሶፍ ኡመር ዋሻ በማድረግ “ኦሮሚያን እናስተዋውቃት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ጉብኝት ለአራት ቀናት ይቆያል።

የአለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ  የክልሉ የመስህብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ የጉብኝቱ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ሁሉም እንዲጎበኝ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በጸጥታ ችግር ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ  ጠቁመዋል።

በኢትዮ ቱሪዝም፣ በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ትብብር የተዘጋጀው ይህ ጉብኝት በክልሉ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ያስተዋውቃል።

ጉብኝቱ በኦሮሚያ ካሉት አምስት መዳረሻ መስመሮች የስምጥ ሸለቆና ባሌ ሶፍ ኡመር ዋሻን እንደሚያካትት ኢዜአ ዘግቧል።

የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች፣ የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ የሀረና ደንና የሶፍ ኡመር ዋሻ እንደሚጎበኙ ታውቋል።

በጉብኝቱ ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአስጎብኚ ድርጅቶች እንዲሁም ከዘርፉ የተውጣጡ የሚመለከታቸው አካላትና የሚዲያ አካላት እየተሳተፉ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.