Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል መከሰቱን ኮሚሽኑ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተ የፀጥታ መደፍረስ የተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባሕርያትን የሚያሟሉ መሆናቸውን በምርመራ ሪፖርቱ አመለከተ።
ኮሚሽኑ ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በነበሩ ሦስት ተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የባለሞያ ቡድኖቹን ወደ 40 የክልሉ አካባቢዎች የላከ ሲሆን፣ የምርመራውን ግኝቶች ታኅሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።
በ59 ገጽ ሪፖርቱ እንዳመላከተው በጥቃቱ የተሳተፉት ብዙ ቁጥር ያላቸው እና ከቦታ ቦታ በቡድን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡
በተፈፀሙ ጥቃቶች የ123 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ500 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል ብሏል ኮሚሽኑ በሪፖርቱ።
በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ፣ በብሔርና በሃይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሲቪል ሰዎችን፣ ቢያንስ በ40 የተለያዩ ቦታዎች በተስፋፋና ለሦስት ቀናት በቆየ ሁከት ማጥቃታቸው፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደሚያደርገው የኮሚሽኑ በግኝቴ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
ምንም እንኳን የፀጥታ ኃይሉ በየቦታው የገጠመውን መጠነ ሰፊ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እና የፀጥታ አባሎቹንም የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ሁኔታ በመሰማራታቸው ኃላፊነታቸው እጅግ ፈታኝ የነበረ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ብሏል፡፡
ይሁን እንጂ በተወሰኑ ቦታዎች የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ፣ ሰልፍ ውስጥ ያልነበሩ፥ በመንገድ ወይም በቤታቸው በር ላይ የተገደሉ፣ ለማሸማገል ጣልቃ የገቡ የአገር ሽማግሌዎችን እና የአዕምሮ ህመምተኛ ጭምር እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል ነው ያለው።
ኮሚሽኑ አጥፊዎቹ ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው ሲልም በመግለጫው ጠይቋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.