Fana: At a Speed of Life!

በከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከተሞች ለሰላም እጦት መንስኤ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

“ሰላም ለከተሞች” በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ከተሞች የፓናል ውይይት በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን ፕሬዚዳንቷ በፎረሙ ላይ የፍትህና ተጠያቂነት መጓደልና ስራ አጥነት በከተሞች የሚስተዋሉ ዋና ዋና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት ከህዝቡ ጋር በግልጽ ውይይት መደረግ እንዳለበት የተናገሩ ሲሆን÷የከተሞች ሰላም ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በፖሊሲ ሊደገፍ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

በተለይ ከተሞች የዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ዋነኛ ምንጭ መሆን አለባቸው ያሉት ፕሬዚዳንቷ አካታች ልማትን በማስፈን የሰላማዊ መስተጋብር ተምሳሌት ሊሆኑ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ።

የሰላም እጦት ስራ አጥነትን በማምጣት የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ እንደሚያዛባም ጠቁመዋል ።

ለዚህ ችግር ትልቁ መፍትሔ የከተሞችን ሰላም በማረጋገጥ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ልዩነት ማጥበብ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጸዋል።

በከተሞች ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባራትን በማረጋገጥ፣የገጠርና ከተማውን ማህበራዊ ትስስርና የምርት ሰንሰለት በማጠናከር ፣የኑሮ ልዩነት አለመመጣጠን እንዲጠብ በማድረግ ረገድም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል ፕሬዚዳንቷ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንበጣ መንጋን በመከላከልና ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም በማቋቋም በኩል ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ ሙሀመድ በበኩላቸው የከተሞች ልማት ከሰላም ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቁመው ፡፡

ከተሞች የሀገራችንን መልካም ገጽታዎች የሚያጠለሹ ድርጊቶችን በመዋጋትና የጋራ እሴቶቻችን ይበልጥ እንዳይሸረሸሩ በማድረግ በኩል አርኣያ መሆን እንደሚገባም ሚኒስትሯ ማሳሰባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሀይለማሪያም ተስፋዬ ደግሞ የከተሞች ሰላም ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ መሆኑን ጠቁመው መቻቻልና አብሮነትን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች የከተሞችን ልማት የሚያጓትቱበት ሁኔታ መቀረፍ አለበት ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.