Fana: At a Speed of Life!

በካማሺ ዞን ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ ህዝቡ በሙሉ አቅሙ ሊተባበርና ከጸጥታ አካላት ጎን ሊቆም ይገባል-አቶ አሻድሊ ሃሰን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የካማሺ ዞንን ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የዞኑ ሕዝብ በሙሉ አቅሙ ሊተባበርና ከጸጥታ አካላት ጎን ሊቆም እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ተናገሩ፡፡
 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የጸጥታ አካላት በካማሺ ዞን ዘላቂ ሰላምን ማስከበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይት መድረኩም የካማሺ ዞን የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት፣ ምርታማ እና ከዓመታት በፊት ደግሞ ሠላማዊ አካባቢ እንደነበር ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ተናግረዋል፡፡
 
በዞኑ ያለውን የድንጋይ ከሠል የተፈጥሮ ሃብት የዞኑ ነዋሪዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲጠቀሙ እየተደረገ ባለበት ወቅት ከህወሓት አጀንዳ ተቀብለው ሕዝቡን ነጻ እናወጣለን የሚሉ ኃይሎች የዞኑን ሠላም ማደፍረሳቸውን አንስተዋል፡፡
 
ከለውጡ ወዲህ የካማሺ ዞን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ የነበረውን የመንገድ መሠረተ-ልማት ለመገንባት በጀት ቢያዝም፣ ከዞኑ ማኅበረሰብ ወጥተው ወደ ጫካ በገቡ ጸረ-ሠላም ኃይሎች መስተጓጎሉን ነው የገለጹት፡፡
የዞኑ ሕዝብ በዚህ ጸረ-ሠላም ኃይል በርካታ ግፍ ደርሶበታል ያሉት አቶ አሻድሊ÷ ከአሁን በኋላ ግን ይህ ግፍ አይቀጥልም ብለዋል፡፡
 
መንግስት የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ጠቅሰው÷ ወደ ጫካ የገቡ የጸረ-ሠላም ኃይሉ አባላት በአጭር ጊዜ ውስጥ እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በካማሺ ዞን ዘላቂ ሠላም ለመገንባት በሚደረገው ጥረትም የዞኑ ሕዝብ ከልቡ እንዲተባበርና ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
 
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው÷ በካማሺ ዞን የክፋትን ጥግ እየፈጸመ ያለውን የህወሓት ተላላኪ ቡድን ለመደምሰስ የዞኑ ሕዝብ “ከእንግዲህ በቃ” ብሎ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን ሊቆም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
 
የሽፍታ ቡድኑ እስካሁን በህዝቡ ላይ ያደረሰው መከራ ይበቃል ያሉት አቶ ገዱ÷ የሽፍታ ቡድኑን ዕድሜ ለማሳጠር ህብርተሰቡን ጨምሮ በተቀናጀ መንገድ መዝመት እንደሚገባ በመጠቆም መንግስትም ለዚህ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
 
ከራሱ ማኅበረሰብ ወጥተው ሠላሙን የሚያውኩ እነዚህን አካላት እጃቸውን እንዲሰጡ አልያም እንዲደመሰሱ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠበቅበትም ጠቅሰዋል፡፡
 
በውይይቱ ላይ የተገኙ የካማሺ ዞን የሃገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች÷ በጉሙዝ ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን የጉሙዝ ማኅበረሰብን የማይወክሉ የጥፋት ኃይሎች እያደረሱብን ያለው ጥቃት ይበቃል ብለዋል፡፡
 
ችግሩን በሠላማዊ መንገድ በሃገር ሽማግሌዎች ለመፍታት ጥረት ቢደረግም አልተቻለም ያሉት ነዋሪዎቹ÷ በንጹሃን ዜጎች ላይ ግልጽ ጦርነት የከፈቱ የጥፋት ኃይሎችን ከዚህ በኋላ እሹሩሩ ማለት እንደማይገባ ማሳሰባቸውንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.