Fana: At a Speed of Life!

በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የወታደራዊ ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ብርጋዴር ጀኔራል ኪዱ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የወታደራዊ ከፍተኛ መኮንን ብርጋዴር ጀኔራል ኪዱ አለሙ ፍርድቤት ቀረቡ፡፡

ተጠርጣሪው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡ ሲሆን መርማሪ ፖሊስም የሰራቸውን የምርመራ ስራዎች ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪው ኬኒያ ሆነው የኦነግ ሸኔ አባላትን ሲመለምሉና ስልጠናም ሲሰጡ እንደነበር ለችሎቱ የገለፀው መርማሪ ፖሊስ ከህወሓት የፀረሰላም ቡድን ጋርም ተልዕኮ ተቀብለው በዚያው በኬኒያ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር በማስረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በመኖሪያ ቤታቸው ባደረኩት ምርመራ የተለያዩ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ያላቸው የባንክ ደብተሮች፣ ኤሌክትሮኒክሶች እንዲሁም በእጃቸው የተገኙ ሞባይሎችን ለቴክኒክ ምርመራ ለሚመለከተው አካል ልኬያለሁ ብሏል::

ቀረኝ ባላቸው የምርመራ ስራዎቹ የእርሳቸውንና የምስክር ቃል መቀበል፣ በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በተፈፀሙ ወንጀሎች የአስከሬን ምርመራ ውጤት ማስመጣት እና ሌሎች ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ 14 ቀናት ያስፈልገኛል ብሏል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቃም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 19 ንዑስ ቁጥር 3 ጊዜ ቀጠሮን በተመለከተ በቂ ምክንያት ሊኖር ይገባል ነው የሚለው ሲል ተጨማሪ የጊዜ ጥየቃን ተቃውሟል፡፡

የአስከሬን ምርመራን በተመለከተ እሳቸው ያላቸው ግንኙነት የለም፣ ስለዚህም ተጨማሪ ጊዜ ሊጠየቅ አይገባም፤ ቃላቸውንም እስካሁን መቀበል ይገባው ነበር ሲል በዋስ ወጥተው ከውጭ ቢከታተሉ ማስረጃዎችን ሊያሸሹ አይችሉም ሲል ተከራክሯል፡፡

ብርጋዴር ጀኔራል ኪዱ በበኩላቸው የአስም ህመምተኛ መሆናቸውን ገልፀው ከመጋቢት 2011 እስከ ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም በኬኒያ ኤምባሲ በስራ ላይ ነበርኩ፤ ተመለሱ ሲባል ነው የመጣሁት ወንጀል ቢኖርብኝ በዚያው መጥፋት እችል ነበር፤ በመኖሪያ ቤቴ 2 የባንክ ደብተርና ለስራ የምጠቀምባቸው የራሴ ሞባይሎች ናቸው የተገኙት ፍርድ ቤቱም በዋስ እንዲለቀኝ እጠይቃለሁ ሲሉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

ጉዳዩን ያየው ፍርቤትም በዋስ ቢወጡ ምርመራውን ሊያደናቅፉ ይችላሉ ሲል 13 ተጨማሪ ቀናትን ለፖሊስ ፈቅዷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.