Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥቶት ይሰራል- አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ የመልካም አስተዳደር እና የሰላም ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደሚሠራ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ የክልሉን የ100 ቀናት ዕቅድ የሚያዝያ ወር አፈፃፀም ገምግሟል።
በዚህም በግብርና የመኸር ዝግጅት የእርሻ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው፣ በክልሉ የሜካናይዜሽን እርሻን ተግባራዊ ለማድረግ ትራክተር እየቀረበ መሆኑ ተነስቷል፡፡
በጸጥታ ችግር ምክንያት በሁሉም ዞኖች የግብርና ስራዎች እኩል እየተሰሩ እንዳልሆነ እና በተለይም በካማሼና ማኦ ኮሞ ዞኖች ለልማት ጣቢያ ሰራተኞችና ለአርሶ አደሮች ፈታኝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የጸጥታ ችግሩ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይም ጫና መፍጠሩና ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብአቶችን ለማቅረብ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩም ተጠቁሟል።
ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በተጨማሪ በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር የነዳጅ አቅርቦት ችግርም እንደፈጠረም በግምገማው ቀርቧል።
ይህን አጋጣሚ አላግባብ በመጠቀም በህገወጥ ድርጊት የተሰማሩ ግለሰቦችም ነዳጅን በህገወጥ መንገድ በመሸጥ እጥረቱ እንዲባባስ ማድረጋቸው እና በተደረገ ክትትልም 52 በርሜል ነዳጅ ከስምንት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል፡፡
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውና ባልተገባ ድርጊት የተሳተፉ 82 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱም ነው የተገለጸው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የሕዝብ ቅሬታ ምንጭ ለሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.