Fana: At a Speed of Life!

በክልሎቹ አዋሳኝ የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍታት የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑ ነው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍታት የህዝቦችን ወንድማዊ ግንኙነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የአስተዳደርና ጸጥታ አካላት አስታወቁ፡፡

በክልሎቹ አጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በምስራቅ ባሌ ጊኒር ከተማ ተካሄዷል፡፡

ከኦሮሚያ ምስራቅ ባሌ ዞን የራይቱ፣ ለገ ሂዳና ሰዌና ወረዳዎች እንዲሁም ከሱማሌ ክልል  የሰላሃድና ለገሂዳ ወረዳዎች የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት በምክክር መድረኩ ተሳትፈዋል።

በአጎራባች ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጦሽና መጠጥ ውሃን መሰረት አድርገው የሚከሰቱ ግጭቶችን በውይይት በመፍታት በህዝቦች መካከል የተሻለ ግንኙነት መፍጠርን ዓላማ በማድረግ የምክክር መድረኩ መካሄዱ ተነግሯል።

የሱማሌ ክልል ሰለሃድ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱልፈታህ ሲራጅ እንደገለጹት ከዚህ በፊት አልፎ አልፎ በወሰን አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች በየጊዜው በሚደረጉ ውይይቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን ነው ያስታወቁት።

በምስራቅ ባሌ ዞን የሰዌና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡስማን አብዱልወሃብ በበኩላቸው በየጊዜው በሚካሄዱ የምክክር መድረኮች በአጎራባች ቀበሌዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን በውይይት በመፍታት በአካባቢው የሰላም ቀጠና ለመፍጠር ምቹ መደላድል እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሞና ሱማሌ ህዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረና የተዋለደ ወንድማማች ነው ያሉት ደግሞ የምስራቅ ባሌ ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር በዳኔ ሊበን ናቸው፡፡

ያለውን አብሮነት ለማስቀጠል በሁለቱ ህዝቦች መካከል የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር በውይይቱ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም አንስተዋል፡፡

በሱማሌ ክልል የኤረር ዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ አሊ ከዚህ ቀደም በአዋሳኝ አካባቢዎች ይስተዋሉ የነበሩ ግጭቶች በኦሮሞና ሱማሌ ህዝብ ሽፋን የሚከሰቱ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ግጭቶቹ  የሶስተኛ አካል ፍላጎትና ሴራ እንደነበሩ ባለፉት ሁለት ዓመት በአካባቢው ላይ በተፈጠረው ሰላም መለየትና ማረጋገጥ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ለወደፊቱ የጋራ እቅድ አውጥተን ለሰላም ትኩረት በመስጠት እየሰራን እንገኛለን፤ በተለይም ለጥቃቅን ጉዳዮች ግጭት መነሳት እንደሌለበት ተስማምተናል” ብለዋል።

የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም በበኩላቸው የአጎራባች ህዝቦችን  ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የምክክር መድረኩ  በሁለቱም ክልሎች በየሶስት ወሩ እንደሚካሄድ ነው ያስታወቁት፡፡

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት አጎራባች ወረዳዎችን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.