Fana: At a Speed of Life!

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት የተለያዩ ከተሞችን ከአሸባሪው ሕወሐት ነጻ ማውጣቱን ቀጥሏል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት፣ በ”ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” ባካሄደው ኦፐሬሽን፣ የተለያዩ ከተሞችን ከአሸባሪው ሕወሐት ነጻ የማውጣቱንና በጥልቀት በመግባት የአሸባሪውን ጀሌዎች የመማረክና የመደምሰስ ተግባሩን ቀጥሏል።

በዚህም መሠረት በጋሸና ግንባር ቀውዝባና ጭላ ከተሞችና አካባቢያቸው ከአሸባሪው ኃይል ነጻ የወጡ ሲሆን፣ በወረኢሉ ግንባር በተደረገው ኦፐሬሽን ደግሞ አጅባር፣ ተንታ እና ዶባ ከተሞችና አካባቢያቸው ነጻ ወጥተዋል።  በተያያዘም በከሚሴ ግንባር  ማጀቴን፣ ጭረቲን፣ ከሚሴን፣ ርቄን፣ ወለዲን፣ አልቡኮ ከተሞችን እና የቃሉ ወረዳን አብዛኛውን ክፍል በመቆጣጠር፣ ጥምር ጦሩ ወደ ኢንዱስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ እየገሠገሠ ይገኛል።

ዛሬና ትናንት በተደረጉት ከፍተኛ የማጥቃት ኦፐሬሽኖች አብዛኛው የአሸባሪው ኃይል ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲበተን ተደርጓል። ጥምር ጦሩ በጥልቀት በመግባት የተበተነውን አሸባሪ በመልቀም ላይ ሲሆን አብዛኞቹ ጀሌዎች ሲደመሰሱ ቀሪዎቹ እጅ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በዚህ ኦፐሬሽን አማካኝነት “ተደናብሮ የገባው አሸባሪ ኃይል፣ የዘረፈውን ንብረትና ራሱን ይዞ አይወጣም” ተብሎ የተገባው ቃል በተግባር ተፈጽሟል።

አስቀድሞ ነጻ በወጡት በምሥራቅ፣ በምዕራብና በመሐል ግንባር በሚገኙ ከተሞችና አካባቢዎች መንግሥታዊ አስተዳደር ተመልሶ በመደራጀት ሥራውን ጀምሯል።

የአሸባሪው ሕወሐት ጀሌዎች በጠንካራው የወገን ጦር አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው እየተበተኑና እየተደመሰሱ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ራሱን በማደራጀት አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ ጀሌዎቹን እንዲማርክ፣ እምቢ ያሉትንም እንዲደመስስ፣ የዘረፈውን ንብረትና ትጥቅ እንዳይወጣ እንዲያስቀር መንግሥት ጥሪ አድርጓል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.