Fana: At a Speed of Life!

በኮሮኖ ቫይረስ ከተጠቁ ሀገራት የመጡ 465 ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው – የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 125 ሺህ 850 የሚሆኑ መንገደኞች በሙቀት ልየታ ማለፋቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ 3 ሺህ 538 መንገደኞች ቫይረሱን ሪፖርት ካደረጉ ሃገራት የመጡ መሆናቸውን አስታውቋል።

አሁን ላይም 465 የሚሆኑት ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሶ፥ እስካሁን ባለው መረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ አልተከሰተም ብሏል።

ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ 51 ጥርጣሬዎች ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሰው በሁሉም ጥቆማዎች ላይ ማጣራት ተደርጓልም ነው ያለው።

በተደረገው ማጣራትም 16ቱ የበሽታውን ምልክት በማሳየታቸው እና የቻይና ጉዞ ታሪክ ስላላቸው በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲቆዩ መደረጉንም ገልጿል።

በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉ ነው የተገለፀው።

ቫይረሱን ለመለየት በሚደረገው ሂደትም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚውሉ የተለያዩ ግብዓቶች ለጋንዲ ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲደርስ መደረጉም ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የየካ ኮተቤ ሆስፒታል እና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ባለሙያዎች ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል የትግበራ ልምምድ ማድረጋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.