Fana: At a Speed of Life!

በኮቪድ-19 ምክንያት ተራዝሞ የነበረው ሀገራዊ ምርጫ አሁን ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ማካሄድ እንደሚቻል የጤና ሚኒስቴር ምከረ ሀሳብ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮቪድ 19 ምክንያት ተራዝሞ የነበረው ሀገራዊ ምርጫ አሁን ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ማካሄድ እንደሚቻል የጤና ሚኒስቴር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሀሳብ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎችን በሚመለከት ለምክር ቤቱ ሪፖርት እና ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

በቀረበው ሪፖርት እና ምክረ ሀሳብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እየቀነሰ ባይሆንም የቅድመ መከላከል እና ስርጭቱን በመግታት ሂደት ውስጥ በሁሉም ደረጃ አቅም ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሁሉም ክልሎች የተሰራጨ ሲሆን፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 በሽታ ከተገኘባቸው ውስጥ 95 በመቶ የታወቀ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል።

እስከ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 1 ሚሊየን 165 ሺህ 647 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በዚህም 66 ሺህ 224 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን እና 1 ሺህ 45 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉንም አስታውቀዋል።

አሁን ላይ የመመርመሪያም ሆነ ክትትል የማድረጉ አቅም በማደጉ በነሃሴ ወር ብቻ ከፍተኛ የሚባል ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ቤት ለቤት መጎብኘት መቻሉን እና ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን መለየት እንዲሁም ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ማከናወን መቻሉንም በሪፖርቱ ላይ አብራርተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን በተሻለ ከማወቅ በተጨማሪ የመከላከል እና የመቆጣጠር አቅምን በከፍተኛ ደረጃ መፍጠር መቻሉንም ገልፀዋል።

ከእነዚህ ውስጥ አመራሩ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉ፣ በሚዲያ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መከናወኑ፣ የቅኝት ስራ ላይ የሚያስፈልጉ አደረጃጀቶችን ማስፋት መቻሉ እንዲሁም ከ10 ሺህ 500 በላይ የድንገተኛ ምላሽና የበሽታ ቅኝት የሚከናውኑ ቡድኖችን ማደራጀት መቻሉንም አስታውቀዋል።

የላቦራቶሪ ናሙና መሰብሰቢያ ቦታዎችን በየወረዳው መስፋት መቻሉንም በሪፖርታቸው አንስተዋል።

የምርመራ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል ያሉት ዶክተር ሊያ፥ የጤና ተቋማትና የአልጋ ቁጥር ማሳደግና የቤት ውስጥ ህክምና አገለግሎት ማስጀመር መቻሉንም አንስተዋል።

የመመርመሪያ ኪቶች ማምረቻም ማቋቋም እንደተቻለም በሪፖርታቸው ላይ አቅርበዋል።

በዚሁ መሰረት የቀጣይ ወራት ትንበያ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር፣ የሞት ቁጥር እና ወረርሽኙ ከፍተኛውን ጣሪያ የሚደርስበት ጊዜ በዋናነት የሚወሰነው በአካላዊ መራራቅ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምበል በሚተገበርበት ደረጃ ነው ብለዋል።

ለምሳሌ ያክል አካላዊ ርቀት 5 በመቶ እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ 50 በመቶ የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ መተግበር ከተቻለ ምንም አይነት እርምጃ ባይወሰድ ሊደርስ ከሚችለው የበሽታ ስርጭት እና ሞት አንጻር በ92 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል ተመላክቷል።

እነዚህና ሌሎችም ነጥቦችን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ እርምጃዎች ሲወሰዱ የቆዩ ሲሆን፥ በቀጣይም በተሻለ ደረጃ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በዚሁ መሰረት ሀገራዊ ምርጫን የማካሄድ ሂደት ውስጥ በርካታ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ምልከታ የተደረገባቸው ሲሆን፥ በአንዳንዶቹ በወረርሽኝ ወቅት ምርጫ ተካሂዷል፤ በአብዛኞቹ ደግሞ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

በኢትዮጵያም በሽታውን የመከላከልም ሆነ የመቆጣጠር ዝግጅነቱ ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት ምርጫን ማከናወን ስጋቱ የበለጠ የሚያሳድገው በመሆኑ በተላለፈው ውሳኔ እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

ወረርሽኙ አሁንም የጤና ስጋት ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበሩት ልምዶች እንፃር ከፍተኛ አለመሆኑ፣ ኮቪድ-19 በሽታ ረዘም ላለ ጊዜ አብሮን ሊቆይ ስለሚችልና አንፃራዊ በሆነ ሰዓት ምርጫው ሲራዘም ከነበርንበት ሁኔታ ለስርጭቱ የተሻለ መረጃ ያለን በመሆኑ ቀደም ሲል ከነበረበት በተሻለ የመከላከል ሁኔታዎች በመኖራቸው፣ የህብረተሰቡ ግንዛቤ መሻሻል በማሳየቱ፣ የማስክና የሳኒታይዘር ምርት በሀገር ውስጥ በስፋት በመኖሩ፣ የጤና ተቋማት ዝግጁነት እና ግብአት አቅርቦት መሻሻሉ፣ የምርመራ ኪት ማምረትን ጨምሮ የላቦራቶሪ አቅም ማደግና የዘርፈ ብዙ ምላሽ በተሻለ ሁኔታ የሚገኝ መሆኑ እንዲሁም የሀራት የምርጫ

ተሞክሮን በማየት የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ሀገራዊ ምርጫን ማካሄድ ይቻላል።

ከዚህ በፊት ከነበረው የምርጫ ሂደት በተለየ መልኩ ኮቪድ-19ኝ መከላከልን ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ እና ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን ማዘጋጀትና በተዘጋጁ ዝርዝሮች መሰረት በሁሉም ደረጃ በበቂ ዝግጅቶች ወደ ትግበራ መግባት ያስፈልጋልም ይላል ምክረ ሃሳባቸው።

በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የወረርሽኝ ስርጭት ከተከሰተ በተለየ ሁኔታ መታየት ሊያስፈልግ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀት ያስፈልጋል ሲል ሚኒስቴሩ ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል።

ከትምህርት ጋር በተያያዘም ዓለምአቀፉ የጤና ድርጅት ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች  በመተግበር እንደየአከባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ትምህርት ቤቶችን መክፈት የሚቻል መሆኑንም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ግን እነዚህን መስፈርቶች በአግባቡ መከናወናቸው የሚያረጋግጥ ግብረ ኃይል በየትምህርት ቤቶቹ ሊቋቋም እንደሚገባም አሳስበዋል።

ምክር ቤቱም በቀረበው ሪፖርትና እና መክረ ሀሳብ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር እይታ በዋናነት የሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

 

በሀይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.