Fana: At a Speed of Life!

በኮድ ሁለት ሲሰሩ የነበሩ የዶልፊን ቫን ተሽከርካሪዎች ጥያቄ ምላሽ አገኘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2008 ዓ.ም ባገለገሉ የዶልፊን ቫን ተሽከርካሪዎች የታሪፍ ውዝግብ ምክንያት ኤክሳይስ ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ያቀረቡት ቅሬታ መፈታቱን የጉሙሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

ተሽከርካሪዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ በገቡበት ወቅት በተሰጠው የመፍትሄ ሃሳብ መሰረት የህዝብ ወይም የጭነት አገልግሎት እየሰጡ በኮድ ሶስት እንዲስተናገዱ ተወስኖ ነበር።

ሆኖም ከውሳኔው ውጭ በሆነ መንገድ በኮድ ሁለት ሰሌዳ ሲንቀሳቀሱ በመገኘቱ ኮሚሽኑ ህጋዊ እርምጃ ወስዷል።

የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ፥ ምንም እንኳን ባለንብረቶቹ የተወሰነውን ውሳኔ የተላለፉ ቢሆንም ኮሚሽኑ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተሽከርካሪዎቹን ወደ ኮድ ሶስት ወይም ኮድ አንድ እንዲቀይሩና የህዝብ ወይም የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ ጊዜ በመስጠት ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ አስቀምጧል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ህግ በማስከበር ሂደት የተወሰኑ ተሽከርካሪዎችን በያዘበት ጊዜ የቀረበውን ቅሬታ በመመልከት ምንም እንኳን ቅሬታ አቅራቢዎቹ የያዙት ዲክላራሲዎን ላይ ተሽከርካሪዎቹ ለህዝብ ወይም ለዕቃ መጫኛ የሚውሉ መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም ሁለተኛ እድል መስጠቱንም ገልጸዋል።

የተሰጠው እድል የመጨረሻ መሆኑን የገለጹ አቶ ደበሌ፥ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ድርጊቶች ቢፈጸም ኮሚሽኑ ሳይከፈል የቀረውን ኤክሳይዝ ታክስ እንደሚያስከፍል መገለፁን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.