Fana: At a Speed of Life!

በወላይታ ዞን በህዝብና በመንግስት መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር እየሰሩ ነው ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በወላይታ ዞን የህዝቡ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዳይመለስና በህዝብና በመንግስት መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር ለውጡን ከማይደግፉ አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ ነው ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ፡፡

የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ከትናንት ጀምሮ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉት አካላት እየተነሳ ያለውን የክልል እንሁን ጥያቄ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንዳይፈታ ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ 10 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የማጣራት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አመራሮቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በአካባቢው መንገድ የመዝጋትና ግርግር የመፍጠር አዝማሚያ መታየቱንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና ሌሎች ደግሞ መቁሰላቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይም አካባቢው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲመለስ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በደቡብ ክልል የተነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች መንግስት ባስቀመጠው ህጋዊ መንገድ እየተመለሱ እንደሚሄዱ የተናገሩት አቶ አለማየሁ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠብቅና ህገ ወጥ ከሆኑ አካሄዶች እንዲቆጠብም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.