Fana: At a Speed of Life!

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ህዝቦች ከሁለት ዓመታት በፊት ግንባራቸውን ለጥይት፣ ደረታቸውን ለጦር ሰጥተው አደባባይ የወጡት የይስሙላ ፌዴራሊዝም ወገባቸውን አጉብጦት፣ ተስፋቸውን አጨልሞት ነው፡፡ ጥቂቶች ዜጎችን እያፈኑና እነርሱ እየከበሩ መምጣታቸው ቁጣቸውን አገዘፈው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ሆና ለማየት ከሚያልሙት እጅግ እየራቀ መምጣት የቁጣቸውን ኃይል አገዘፈው፡፡

እውነተኛ የፌዴራል ስርዓትን ለመተግበር ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ዜጎች በጋራ የሚሳተፉበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መሰረቶች ተግባር የራቃቸው የቃል ተረቶች ሆነው መቆየታቸውም የቁጣቸውን ኃይል ከፍ አድርጎታል፡፡ ኢህአዴግ በፌዴራሊዝም ካባ ሲንቀሳቀስ ዜጎች በአገራቸው ቀርቶ በራሳቸው ጉዳይ እንኳን መወሰን የሚችሉበትን እድል ተነፍጓቸው ቆይቷል፡፡ በዚህም በግንባር ታጥረው፣ በአጋርነት ተገድበው ዓመታትን በቁዘማ አሳልፈዋል፡፡

ለዚህም ነው የህዝብ ብሶት ገንፍሎ፣ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ የለውጥ ፍላጎት ተቀጣጥሎ ከተፈጠረው ለውጥ ማግስት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸውም፣ በአገራቸውም ጉዳይ ተሳታፊና ወሳኝ የሚሆኑበት እውነተኛ ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲ ብርሃን መፈንጠቅ የቻለው፡፡

ይሁን እንጂ ይህን የብርሃን ፍንጣቂ ለዜጎች የብልጽግና መስመርን ሲያመላክት፣ በቃል በታጠረው የኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ስም ሲዘርፍ፣ ሲገርፍና ሲገድል የነበረው የህወሃት የጥፋት ቡድን ከሌብነትና ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ተግባሩ ገድቦታል፡፡ በህዝብ ሞትና እንግልት የመክበርና የራስ ጥቅምን የማስቀጠል ጉዞንም ዘግቶበታል፡፡ ይህ የጥፋት ኃይል ከለውጡ ጋር ተጣጥሞ መጓዝ ባለመቻሉ ራሱን ከለውጡ ጉዞ በማውጣት የቀድሞ የበላይነቱን፣ የዘረፋና የአፈና ሥርዓቱን ለማስቀጠል የሞት ሽረት ትግሉን ሲያካሂድ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

በህውሃት ስም የሚንቀሳቀሰው የጥፋት ቡድን የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ በማስቀደም አገርን ለከፋ አደጋ አጋልጧል፡፡ በተለይም ሕዝቡን በብሔር በማቧደን፣ እርስ በርሱ እንዳይተማመን በማድረግና በማጋጨት የአገር ሰላም እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ በማንነት ስም ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምስል እንዲደበዝዝ ድብቅ ሴራ ሲያራምድ ቆይታል፤ እያደረገም ነው፡፡ ከአንድነት ይልቅ የብተና ፖለቲካ በማራመድ ህዝብን እርስ በርስ በማጋጨት ለግጭትና መፈናቀል ዳርጓል፡፡

የአገራችን ህዝቦች ለዘመናት የናፈቁት ዴሞክራሲ እንዳይኖርና እንዳይገነባ አድርጓል፡፡ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ዜጎችም እስር፣ እንግልትና ወከባ ተፈጥሮባቸዋል፤ ግርፋትና የኢ-ሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች ተዳርገዋል፡፡ ቆስለዋል፣ አካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሞተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በህወሃት ስም የሚንቀሳቀሰው የጥፋት ሃይል ዋነኛ ተጠያቂ መሆኑ ለአገራችን ሕዝቦች የተሰወረ ምስጢር አይደለም፡፡

እንደእውነቱ የአገራችን ህዝቦች ለሰው ልጆች ያላቸው ክብር ዓለም የመሰከረለት ነው፡፡ ለዘመናት በታሪካቸው ማህደር ውስጥ የሰፈረው እውነት የሚያረጋግጠው እንግዳ ተቀባይነታቸውና ሰው አክባሪነታቸው፣ ለሰው ልጆች ህይወት ትልቅ ትርጉም የሚሰጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ይህን ዓለም ያደነቀውን ታላቅ እሴት አክብረውና ጠብቀው ለመኖር ሌት ተቀን የሚታትሩ ህዝቦችም ናቸው፡፡

ለዚህም ነው ዓለምአቀፍ የሰብዓዊነት ድንጋጌዎችን አክብረውና ተቀብለው የሕገ መንግስቱ የማዕዘን ድንጋይ ያደረጉት፡፡ እነዚህን ድንጋጌዎች በማክበርና በመጠበቅ ግን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በርካታ ተግዳሮቶች ገጥሟቸዋል፡፡

የአገሪቱን ህገ መንግስት፣ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ህግጋቶችን የጣሱ ድርጊቶች የህወሃት የጥፋት ቡድን ሲፈጸም ቆይቷል፡፡ በህግ ጥላ ስር የነበሩ ዜጎች ተገቢውን ፍርድ ከማግኘት ይልቅ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽምባቸው ቆይተዋል፡፡ በጥብቅ ምስጢር ባደራጃቸው የራሱ ቡድኖች አማካኝነት ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡

እነዚህ የሰብዓዊነት ሽታ የሌላቸው የህወሃት የጥፋት ቡድን ከራሳቸው ውጭ የሚያዳምጡት ምንም ጩኽት ባለመኖሩ ለዓመታት ከአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በሰቆቃ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ቤት በሃዘን እንዲሞላ አድርገዋል፡፡  ከልክ ያለፈው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቱ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ስሟ እንዲጠለሽ አድርጓታል፡፡

ይሁን እንጂ የለውጡ መንግስት ይህን አሳዛኝና አሳፋሪ ታሪክ ዳግም በኢትዮጵያ ምድር እንዳይመጣ ተግቶ እየሰራ በሚገኝበት በዚህ ወቅት መንግስትን በተለያዩ ጉዳዮች ውጥረት ውስጥ በመክተት ወደኋላ ለመጎተት ያለማቋርጥ ትንኮሳ እየፈጸመ ይገኛል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

አገራችን በህዝቦቿ ጥረትና ታታሪነት እየገነባች የመጣችው ኢኮኖሚዋ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ መረዳት ይቻላል፡፡ ችግሩ እየሰፋ ድህነቱ እየተባባሰ ዜጎች ከድጡ ወደ ማጡ እየገቡ መጥተው ከጫፍ ላይ ተደርሶ እንደነበር ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡

በርግጥ ከለውጡ በፊት እንደ ሀገር ተፈጥሮ ለነበረው የኢኮኖሚ መዋዠቅ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ቢታመንም፤ ዋነኛው የህወሃት የጥፋት ቡድኑ አባላት የሀብት መቀራመት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በተለይም  ለታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች እንደ ህዳሴ ግድብ፣ የምድር ባቡር፣ ስኳር ፕሮጀክቶችና ማዳበሪያ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሜቴክን ለመሳሰሉ ተቋማት ማስፈፀሚያ የተመደበን የህዝብ ገንዘብ በህወኃት ስም የሚንቀሳቀሰው የሌቦች ቡድን ገንዘቡን በመከፋፈል ወደ ውጭ አገሮች በማሸሽ የተገለጠ ነው፡፡

የአገራችን ሕዝቦች እንደሚያውቁት ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ መንገራገጭ ውስጥ በመግባቱ ለመንግስት ሰራተኞች እንኳ ወርሃዊ ደመወዝ መክፈል አዳጋች ሆኖ ነበር፡፡ ለሀገር ደህንነት እጅግ ወሳኝ የሆነውን ነዳጅና መድኃኒት እንኳ መግዣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲያጋጥማት ሆኗል፡፡ ከሁሉም በላይ በሚያስደንቅና የዝርፊያውን ወሰን ማጣት በሚያመለክት ደረጃ ከውጭ አገራት ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያሥገቡ ግዝፉ መርከቦች በዚሁ ቡድን አማካኝነት መሸጣቸው ለቡድኑ አባላት የነዋይ ፍቅር መስዋዕት መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ይሄን ሁሉ ጥፋት በአገራችን እና በዜጎቻችን ላይ ያደረሰው የህወሓት የጥፋት ቡድን በህዝቦች የለውጥ ሃይል ከተገፋ በኋላ መቀሌ መሽጎ ሌላ ጥፋት እየደገሰና እያደረሰ ይገኛል፡፡

የፌዴራል መንግስት በሆደ ሰፊነት ህጋዊ አካሄድን በማስቀደም ሁኔታዎችን ለማስተካከል ጥረት ቢያደርግም የጥፋት ቡድኑ ከድርጊቱ ሊታቀብ አልቻለም፡፡ በተደጋጋሚ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዜጎችን ህይወት በመቅጠፍ እብሪተኝነቱን በግላጭ አሳይቷል፡፡

የህወሓት የጥፋት ቡድን ከመንግስት አሰራር ውጭ የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም፣ የማዕከላዊ መንግስት ትዕዛዞችን በመጣስ፣ የሰራዊቱን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ጭምር በማስተጓጎል አገራዊ ክህደቱን በተግባር አረጋግጧል፡፡

ይህ የጥፋት ቡድን ከትናንት ወዲያ ምሽትም የአገራችንንና የአህጉራችን ኩራት የሆነው የመከላከያ ኃይላችን ላይ ተኩስ በመክፈት የመንግስትን ቀይ መስመር ጥሷል፡፡ የአገር ሉዓላዊነታችን በመዳፈር አፍሪካዊ ወንድሞቻችንን ጭምር አንገት ያስደፋ እኩይ ተግባር ፈፅሟል፡፡

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ምሁራን

መንግስት በአገራችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የምታበረክቱትን ፋይዳ በሚገባ ይገነዘባል፡፡ ቀደም ሲል እንደ ስጋት ይታይ የነበሩትን የአገራችንን ምሁራን በማቅረብ የአገሪቷ የለውጥ እንቅስቃሴ አጋዥ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡

እንደምትገነዘቡት በአሁኑ ወቅት ከሀዲው የህወሃት ቡድን የኩራታችንና የሉዓላዊነት ምንጭ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊታችን ባልጠበቀው ሁኔታ በመክበብ ጥፋት ለማድረስ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህ ቡድን አገራችንን ለማፈራረስ መቼም ቢሆን ወደኋላ እንደማይል በግልጽ አሳይቷል፡፡

ስለሆነም የአገራችን ምሁራን የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ከመንግስት ጎን በመቆም አገርነታችሁን እንድታሳዩ መንግስት ጥሪ ያስተላልፋል፡፡

የተከበራችሁ የመንግስት ሰራተኞች

የተከበራችሁ በተለየዩ ተቋማት የምትሰሩ የመንግስት ሰራተኞች የህወሓት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ኃይላችን ላይ የፈጸመው እኩይ ተግባርን ተከትሎ መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ በተለያየ መንገድ አጋርነታችሁን ስላሳያችሁ አክብሮታችን ላቅ ያለ ነው፡፡ አሁንም የእለት ተእለት ስራችሁን ሳታስተጓጉሉ በመከወን፣ የጥፋት ኃይሎችን ሴራም አከባቢያችሁን በንቃት በመጠበቅና በመከታተል ከከሀዲው የህወሃት ቡድን ሴራ አገራችንን ለመታደግ የተጀመረውን አገር የማዳን እንቅስቃሴ በመደገፍ ከመንግስት ጎን እንድትሰለፉ ጥሪ ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የፀጥታና ደህንነት ኃይሎች

ለአገራችሁ ሉዓላዊነት መከበርና ለህዝቦች ሰላም መስፈን የራሳችሁንና የቤተሰባችሁን ህይወት አሳልፋችሁ የሰጣችሁ የፀጥታና ደህንነት ኃይሎች እየከፈላችሁት ያለውን መስዋዕትነት መቼም የምንዘነጋው አይደለም፡፡ አሁንም ዜጎችን በመጠበቅና ከጥቃት በመከላከል በተለመደው ጀግንነታችሁ ለአገራችሁ የገባችሁትን ቃል እንደምትጠብቁ፤ የህወኃት ቡድን የማስወገድ ኦፕሬሽን እንደስካሁኑ ሁሉ በአስተማማኝ ድል እንደምትቋጩት ሕዝባችንና መንግስት በጽኑ ይተማመናሉ፡፡

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ሴቶች

የአገራችን ወጣቶችና ሴቶች የህወሓት የጥፋት ቡድን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከስደትና ከችግር ሳያላቅቃችሁ ይልቁንም በስማችሁ እየነገደ ኪሱን ሲያደልብ እንደኖረ መንግስት ይገነዘባል፡፡ መንግስት በዚህ የጥፋት ቡድን የተፈጠረውን ኢ-ፍትሃዊነት ለማስተካከል ጥረት ቢያደርግም በየጊዜው በየአቅጣጫው ቀድሞ ባደራጀቸው አጥፊ ቡድኖች የአገራችንን ሰላም ሲነሳ፤ ወጣቶችና ሴቶችንም የጥፋት ሰለባው ሲያደርግ በግልጽ ታይቷል፡፡

አገራችንን ወደፊት ለማሻገር መንገድ ብንጀምርም ይህ የነፍሰ ገዳይ ቡድን የአገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ተኩስ በመክፈትና የዘረፋ ሙከራ በማድረግ ኢትዮጵያን በግልጽ ለማፍረስ ተንቀሳቅሷል፡፡

በመሆኑም አገራችን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አገርን እንደ አገር የማስቀጠል መሆኑን በመረዳት ከመንግስታችሁ እና መከላከያ ጎን በመቆም የዜግነት ኃላፊነታችሁን እንደትወጡ መንግስት ጥሪ ያደርጋል፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

ጥቅምት 26/2013 ዓ/ም

አዲስ አበባ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.